
Mahibere Kidusan Broadcast Service – ማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት
በሰሜን ኢትዮጲያ ጦርነት በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ለተጎዱ አብያተ ክርስቲያናት ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 6:00 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ሊዘጋጅ ነው።
የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ እና ሌሎች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ዛሬ ግንቦት አምስት ቀን 2015 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።።
በመግለጫውም «የሀገረ ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናት መዋቅሩን ጠብቀው ለማስቀጠል አዳጋች ሁኔታ ላይ ይገኛሉ»ብለዋል።
በሀገረ ስብከቱ በሚገኙት ቆቦ ከተማ፣ራያ ቆቦ ወረዳ እና ግዳን ወረዳን ጨምሮ በአጠቃላይ በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ጦርነቱ የ99 ካህናትን የሞቱ ሲሆን 51 ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ 182 አብያተ -ክርስቲያኖቿ ወድመዋል ።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመግለጫው ቤተ ክርስቲያኗ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ለሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን ተናግረዋል።
ለዚህም የሚረዳ ጉባኤ ሰኔ 25/2015ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የሚመለከተው ሁሉ እንዲተባበርና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ስቃይ እንዲያበቃ አገልግሎቷም እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።
