በድሉ ዋቅጅራ

Bedilu Wakjira  

· እናትና እድሜ (በድሉ ዋቅጅራ)

ዝናቡ ይዘንባል…..

በር ላይ ቆሜያለሁ፣

የደጁ ወጨፎ ያንዘፈዝፈኛል፤

ብልጭታ – መብርቁ፣

ከሰማዩ ጋራ፣

ከመንደሩ ጋራ፣….ይሰነጥቀኛል፡፡

አወይ እናት ማጣት!

አይ ልጅ መሆን መጥፎ፤

ዛሬም ባምሳ አመቱ፣

በደመነ ቁጥር፣

በዘነበ ቁጥር፣……..ደጃፍ ተደግፎ፤

ምን መብረቅ ቢወርድ፣

ምን ቆፈን ቢይዘው፤

‹‹ደጃፍ ላይ አትቁም፣

መብረቅ ትጠራለህ፣

ወጨፎ ይመታሀል፣

ለሊት ታስላለህ፡፡››

ካላለችው እናቱ፤

አይገባም ከቤቱ፡፡

ይኸው ክረምት መጣ፣

ዝናቡ ዘነበ፣

መብረቁ ይወርዳል፤

አድባር ይታረሳል፤

በር ላይ ቆሜያለሁ፤

ሞቴ ላይ ቆሜያለሁ፡፡

ከቆፈኑ በላይ፣

ከመብረቁ በላይ፣ . . . ሳጣሽ ያስፈራኛል፤

እማ ‹‹ግባ›› በዪኝ፣ ድምጽሽ ያድነኛል፡፡

————

ሚያዝያ፣ 2008፤