
ከ 3 ሰአት በፊት
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸው ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ ጥቃት የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላት ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት ጀርመን ለዩክሬን አዲስ የመከላከያ ድጋፍ ማዕቀፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባረጋገጠችበት ወቅት በርሊን ውስጥ በተገኙበት ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በበርሊን ከጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፋ ሾልዝ ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ በሰጡት አስተያየት “በሩሲያ ግዛት ላይ ጥቃት እያደረስን አይደለም” ብለዋል።
ጨምረውም ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተወሰዱብንን ግዛቶች ለማስለቀቅ ለመልሶ ማጥቃት እየተዘጋጀን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ሾልዝ አገራችው ዩክሬንን አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ድጋፍ ታደርጋለች ያሉ ሲሆን፣ 2.7 ቢሊዮን ዩሮ ሚያወጣ መሳሪያ ለመለገስም ቃል ገብተዋል።
ድጋፉም በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ ከባድ የሚሳኤል እና የድሮን ድብደባ እያስተናገደች ላለችው ዩክሬን ሊዎፓርድ የተባለውን ታንክ እና ተጨማሪ ፀረ አውሮፕላን መሳሪያዎች የሚያስታጥቅ ነው።
ዜሌንስኪ ድጋፉ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከተደረጉት ትልቁ ነው ብለዋል።
ዜሌንስኪ አገሬ በሩሲያ ግዛት ጥቃት እያደረሰች አይደለም ቢሉ፣ ሞስኮ ግን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በክሬሚሊን ደረሱ የተባሉ የድሮን ጥቃቶችን ጨምሮ በዩክሬን እየተፈጸሙ ነው ስትል በተደጋጋሚ ትከሳለች።
- የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላከ 6 ሰአት በፊት
- በቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸናፊውን ለመለየት ሁለተኛ ዙር ድምጽ ሊሰጥ ይችላልከ 5 ሰአት በፊት
- “ከእረፍት መልስ ጨዋታችን ተቀባይነት የሌለው ነበር፤ ይቅርታ መጠየቅ አለብን” ሚኬል አርቴታከ 4 ሰአት በፊት
ዩክሬን ግን ይህንን ታስተባብላለች። ሆኖም የተወሰዱባትን ግዛቶች ለማስለቀቅ ኃይል የመጠቀም መብት እንዳላት ትገልጻለች።
ዩክሬን በሩሲያ ቁጥጥር ስር ያሉትን ደቡባዊ እና ምሥራቅ አካባቢዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የተወሰደባትን የክሪሚያ ባሕረ ገብ መሬትን ለማስለቀቅ መዋጋቷን እንደምትቀጥል ተናግራለች።
ፕሬዝዳንቱ በጀርመን ለእሳቸው እና ለዩክሬን ሕዝብ ከአውሮፓ ኅብረት የተበረከተ ሽልማትንም ተቀብለዋል። ሽልማቱ የአውሮፓን አንድንት ለማጠናከር ላደረጉት አስተዋጾ የተበረከተ ነው ተብሏል።
ይህንን ሽልማት ቀደም ብሎ ዊንስተን ቸርችል፣ ፖፕ ፍራንሲስ እና ቢል ክሊንትን ተቀብለዋል።
እስከ እሁድ ድረስ በዩክሬን የተሰሙ ዜናዎች
- የዩክሬን አየር ኃይል 25 ድሮኖችን እና ከሩሲያ ተተኮሱ ያላቸውን ሚሳኤሎችን ማውደሙን ገልጿል። ሆኖም ምሽቱን ሩሲያ ሰፊ የአየር ጥቃት አድርሳለች።
- ባለፉት 24 ሰዓት ሩሲያ ባደረሰችው ጥቃት በዩክሬን ዶኔትስክ ግዛት ስድስት ሰዎች መሞታቸውን፣ 16 ደግሞ መጎዳታቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
- በኼርሶን ግዛትም እሁድ ዕለት በሩሲያ የአየር ጥቃት አንድ ሰው ተገድሏል።
- በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለችው የዩክሬን ግዛት ምሥራቃዊ ሉሃንስክ፣ በሞስኮ በተሰየሙ ሹማምንት ላይ እየጨመረ በመጣው የዩክሬን ወታደሮች ጥቃት ምክንያት በአከባቢው በጊዜያዊነት የሞባይል ኢንተርኔት ተቋርጧል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከጣሊያን ወደ ጀርመን ሲበሩ በሁለት የጀርመን አየር ኃይል ተዋጊ ጀቶች ታጅበው ነበር።
በሮምም የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የጣሊያኑን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናትን አነጋገርዋል። በተጨማሪም ከሮም ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ጋርም ተወያይተዋል።
ዜሌንስኪ በተመሳሳይ ቀን ወደ ፈረንሳይም አቅንተው በፈረንሳይ ቤተ መንግሥት ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የእራት ፕሮግራም ላይ ታድመዋል።
