የተወዳጇና አንጋፋዋ ዘማሪት ሂሩት በቀለ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ
ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2015
(አዲስ ማለዳ)
ከ50ዎቹ መጀመሪያ እስከ 80ዎቹ መጨረሻ ድረስ በጊዜው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት አርቲስቶች መካከል አንዷና ተወዳጅዋ ድምፃዊት፣ የግጥም እና የዜማ ደራሲ የነበረቸው፤ እንዲሁም ከ80ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ሕይወቷ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በዘማሪነት አገልግሎት የተለያዩ የመዝሙር አልበሞችን በመስራት የምትታወቀው የዘማሪት ሂሩት በቀለ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈፅሟል።
የቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይም የሂሩት በቀለ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የሙያ አጋሮች እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የጥበብ አፍቃሪያን ተገኝተውበታል።
ሂሩት በቀለ መስከረም 28/1935 ከእናቷ ተናኜወርቅ መኮንን እና ከአባቷ መቶ አለቃ በቀለ ክንፌ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ሥሙ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደች።
እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፤ በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅትም ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች አዘውትራ ስለምታንጎራጉር፤ ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው ዓለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር።
በዚህ መሰረት በ1951 ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች፡፡ ከዛም በማስከተል ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች።
በ1952 ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ወደ ፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ በመዛወር በቋሚነት የሙዚቃ ክፍል አባል ሆና የተቀጠረችው ሂሩት፤ በፖሊስ ሠራዊቱ ለ35 ዓመት ያህል አገልግላለች።
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት ድምፃዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ሂሩት በቀለ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿም በሕዝብ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እና ለበርካታ ሴት ድምፃዊያንም መነሻ የሆኑ ናቸው።
ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መካከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በአገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሙዚቃ ይገኝበታል።
በ35 ዓመታት የሙዚቃ ቆይታዋ “ሕይወት እንደሸክላ” እና “ኢትዮጵያን” ጨምሮ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን ለሕዝብ ጆሮ ያደረሰችው ሂሩት በቀለ፤ ከእነዚህም መካከል ከ38 በላይ ሙዚቃዎቿ በሸክላ የታተሙ ሲሆን፤ እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ 14 ካሴቶችንም ለአድማጮች አበርክታለች።
ሂሩት በቀለ እናት አገሯ ጥሪ ባቀረበችላት ቦታ ኹሉ በመገኘት የዜግነት ግዴታዋን በብቃት ከመወጣቷም በላይ፤ ኮንጎ ለዘመተው ለኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ቦታው ድረስ በመሄድ ሰራዊቱን የሚያነቃቁ ተወዳጅ ሙዚቃዎቿን አቅርባለች። በደርግ ዘመንም ራሽያን ጨምሮ በተለያዮ በርካታ የሶሻሊስት አገራት በመዘዋወር የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክታለች።
ከዚህም ባሻገር በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ወራሪ ኃይልና በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ከሻቢያ ጋር በተደረገው ጦርነት ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ጦሩ መሀል በመገኘት ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ ግዳጇን መወጣቷን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህልፈተ ህይወቷን ተከትሎ ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሂሩት በቀለ በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት አገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክተውላታል።
ሂሩት በሙዚቃ ዓለም ውስጥ በቆየችባቸው አያሌ ዓመታት ከማህሙድ አህመድ፣ ከዓለማየሁ እሸቴ፣ ከቴዎድሮስ ታደሰ፣ ከመልካሙ ተበጀ፣ ከታደለ በቀለ፣ ከመስፍን ኃይሌ: ከካሳሁን ገርማሞ እና ከሌሎች ስመጥር ድምፃዊያን ጋር በመሆን ስራዎቿን ለህዝብ ሲታቀርብ ቆይታለች።
ከ1987 በኋላም እራሷን ከሙዚቃ ዓለም ያገለለችው ሂሩት ከዘፈን ዓለም ወጥታ ወደ መንፈሳዊ ዓለም በመግባትና፤ የተለያዩ የመዝሙር አልበሞችን በመስራት ለአድማጮች አቅርባለች።
ሂሩት በቀለ ባደረባት ህመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለረጅም ጊዜ ህክምናዋን ስትከታተል ቆይታ፤ ግንቦት 4/2015 በተወለደች በ80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። ሂሩት በቀለ የሰባት ልጆች እናት፣ የአሥር ልጆች አያት እና የሰባት ልጆች ቅድመ አያት ነበረች።
