May 16, 2023 – Konjit Sitotaw 

የሰሜኑ ጦርነት ሕወሓትና የፌደራል መንግሥት ባደረጉት የሰላም ስምምነት መቆሙን ተከትሎ፤ ትግራይን በጊዜያዊነት እንዲመራ የተቋቋመው የጌታቸው ረዳ አስተዳደር አምቡላንሶችን ያለአግባብ ላልተገባ ተግባር በመጠቀም ከሰሞኑ ክስ እየቀረበበት ይገኛል፡፡

በትግራይ ክልል የሕዝብ አምቡላንሶች ላልተገባ አገልግሎት እየዋሉ መሆኑን ዶይቼ ቬለ ነዋሪች ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ሚዲያው ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉ፤ ከጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ የቀሩት አምቡላንሶች ወላድንና ሕሙማንን ወደ ሆስፒታል ከመውሰድ ይልቅ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ለግልና ለድርጅት ሥራ ሲጠቀሙባቸው ማየት እጅግ ይዘገንናል ብለዋል።

ነዋሪዎቹ በአስተያየታቸው “የህዝብ መገልገያ አምቡላንሶች በየመጠጥ ቤቱ ቆመው የወረዳ ባለስልጣናት የሚዝናኑበባቸው መሆኑን ከማየት የከፋ ንቅዘት በሕይወቴ አይቼ አላውቅም” ሲሉም ገልጸዋል።

ወጣት አጀቡ ገብረመስቀል የተባለች የመቐለ ከተማ ነዋሪ “የሐብት እጥረት ባለበት ክልል እንዲህ አይነት አባካኝ አጠቃቀም ተገቢ አይደለም፤ የጌታቸው ረዳ አስተዳደር በአስቸኳይ እነዚህ በየመጠጥ ቤቱ ተገትረው የሚያድሩ አምቡላንሶችን ሰብስበው ወደ ሕዝብ አገልግሎት እንዲመልሷቸው እንፈልጋልን” ስትል ስለሁኔታው አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

የሕወሓት ባለስልጣናት አምቡላንሶችን በየመጠጥ ቤቱ ጭምር አቁመው ሲዝናኑ የሚያሳዩ ምስሎች በማሕበራዊ ድረገጾች እየተሰራጩ መነጋገሪያ ርዕስ ሆነዋል። ከሰሞኑ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙ የወረዳ አስተዳዳሪዎች ወደ መቐለ የተጓዙት የጤና ተቋም አምቡላንሶችን ተጥቅመው መሆኑም ተሰምቷል፡፡