May 16, 2023 

በአማራ ክልል ከልዩ ሃይል መፍረስና ፋኖን ትጥቅ ከማስፈታት ጋር ተያይዞ ለእስር  የተዳረጉ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች የርሃብ አድማ መጀመራቸው ተነግሯል።
እስረኞቹ የርሃብ አድማውን ማድረግ የጀመሩት በአማራ ክልል የሚካሄደውን እስርና አፈና በመቃወም መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ለሮሃ ቲቪ ተናግረዋል።

ከዛሬ ሰኞ ግንቦት ሰባት ጀምሮ እስከ ረቡእ ግንቦት 9 የሚቀጥል መሆኑንም ነግረውናል።

በዚህም ” ሽብር፣ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥራችኃል እየተባለ የአማራ ሙሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና ወጣቶችን እንዲሁም የቀን ሠራተኞችን ማሰር ይቁም” በሚል እነ ረ/ፕ ሲሳይን ጨምሮ 40 የሚሆኑ ታስረው የሚገኙ የአማራ ሙሁራንና ሌሎች እስረኞች ናቸው የርሃብ አድማውን የጀመሩት።

አድማውን አስመልክቶ ስለጉዳዩ ያውቁ እንደሆን ያናገርናቸው የእስረኞቹ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝም ጉዳዩን ከእስረኞቹ ቤተሰቦች ከሰሙ በኋላ ወደ እስር ቤት በማምራት አድማ መጀመራቸውን እንዳረጋገጡ ነግረውናል።