May 17, 2023 – Konjit Sitotaw 

ህወሓት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ ውሳኔው በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ ነው ብሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ህጋዊ ሰውነት የመመለስን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ ህወሓት የቦርዱን ውሳኔ እንደማይቀበል አስታወቀ።

ድርጅቱ ምርጫ ቦርድ ጥር 10/2013 ያስተላለፈውን ውሳኔ ዳግም በማጤን የህወሓት ህጋዊ ሰውነት ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ የድርጅቱ ሃላፊዎች በፓርቲው ሥም መንቀሳቀስ እንዲችሉ እና የድርጅቱ የተወረሱ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች እንዲመለሱ ሚያዝያ 28/2015 በጻፈው ደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 04/2015 ከህወሓት የቀረበለትን የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ የማስመለስ ጉዳይን <<በህግ ተደገፈ ሆኖ አላገኘሁትም።> በማለት አለመቀበሉን አስታውቋል።

ህወሓት የተወሰነው ውሳኔ የደረሰው ግንቦት 07/2015 መሆኑን በመግለጽ፤ በቦርዱ የተሰጠው ውሳኔ ቅቡልነት የሌለውና በፕሪቶርያ የተደረሰው ስምምነትና ህግን መሰረት ያላደረገ መሆኑን ገልጿል።

ህወሓት <<በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የቆየውን አፋኝ ስርዓት በመገርሰስ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ እንዲያብብ፣ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ በማንነታቸው እንዲኮሩና ታሪካቸው እንዲያሳድጉ የሚያስችል ሕገ-መንግሠሰታዊ ዋስትና እንዲረጋገጥ በማድረግ በኩል ደማቅ አሻራ ያለው አንጋፋ ድርጅት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ ‘ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መንገድ መፈታት ባለመቻሉ በ2013 በትግራይ ክልል ደም አፋሳሽ ግጭት ተፈጥሮ እስከያዝነው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ድረስ መዝለቁን አስረድቷል።

ይህን ደም አፋሳሽ እልቂት በተቻለ መልኩ ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶችን ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሰው ህወሓት፤ በአፍሪካ ህብረት፣ በኢጋድ እና በአሜሪካን መንግሥት አሸማጋይነት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካና በኬንያ መንግሥታት አመቻችነት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ድርድር ተደርጎ በሕዳር 23/2022 በፕሪቶሪያ ከተማ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈረሙን አስታውሷል።

<<የፕሪቶሪያው ስምምነት በመሰረታዊነት ማዕከል ያደረገው ሰላም፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ ተጠያቂነት እና ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መመለስ ነው።>> ያለው ህወሓት፤ ከስምምነቱ መፈረም ጀምሮም ህወሓትና የፌደራሉ መንግሥት በጋራና በተናጠል የገቡትን ግዴታና የስምምነቱን ዓላማዎች እየፈፀሙ እንደሚገኙ ገልጿል።

<<ለዚህም አበረታች የሚባል ውጤትና ለቀጣይ ሥራዎች ምቹ ፖለቲካዊ ሁኔታ እየተፈጠረ በመምጣቱ ስምምነቱ ዓለም አቀፍዊ እና አገራዊ እውቅና ተሰጥቶታል>> ያለው ድርጅቱ፤ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ አገራት መንግሥታት እውቅና እና ድጋፋቸውን መስጠታቸውን አስታውሷል።

በሌላ በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ፣ የክልል መንግሥታት እና የከተማ አስተዳደሮች ለስምምነቱ እውቅናና ድጋፍ የሰጡ ህገ-መንግስታዊ አካላት መሆናቸውን በማንሳት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤትም ድርጅቱን ከአሸባሪነት ስያሜ የመሰረዝ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውሷል።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሰረት በፕሪቶርያው ስምምነቱ አንቀፅ 10(1) በተገደነገገው መሰረት የትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር በኹለቱ ወገኖች ስምምነት መመስረቱን የገለጸው ድርጅቱ፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት ዓላማ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ክልሉን እና የክልሉን ህዝብ ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ መመለስ መሆኑን አንስቷል።

በዚህም መሰረት የስምምነቱ ይዘት ተፈፃሚ እንዲሆን የትግራይ ህዝብና ድርጅታችን ህወሓት እንዲሁም ሃላፊነት ያላቸው የፌደራል መንግሥት አካላት ግዴታቸውን ሊወጡ የሚገባ ቢሆንም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የድርጅቱን ህጋዊ ሰውነት የመሰረዝ ውሳኔ እንዲነሳ የቀረበለትን ጥያቄ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የተሰረዘ የፖለቲካ ፓርቲ ተመልሶ ህጋዊ ሰውነት የሚያገኝበት ድንጋጌ ስለሌለ የድርጅታችን ህጋዊ ሰውነት ሊመለስ እንደማይቻል ካፕሪቶርያ ስምምነት ውጪ በሆነ መንገድ ውሳኔው አሳውቆናል>> ብሏል።

ከዚህ በመነሳት <<በቦርዱ የተላለለፈውን ውሳኔ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የማይቀበል፣ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለውን የሰላም ስምምነቱ ትግበራ ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ ከጦርነቱ ወደ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ለሚገቡ ሃይሎች መደገፍ እና ማበረታታት ሲገባ ድርጅቶችን በማፍረስ ቀጣይ ሰላም እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ መሆኑ፣ ለህዝቦቻችን የማይመች እና ለሌሎች ሃይሎችም ተስፋ የማይሰጥ ነው ብሎ ድርጅታችን ህወሓት ያምናል።>> ብሏል።

ህወሓት ውሳኔው እንደማይቀበለው እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚወያይበት ያሳወቀ ሲሆን፤ የምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንደገና በማጤን የፕሪቶርያ ስምምነትና ሌሎች የፌደራል ተቋማት ያስተላለፉትን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ እንዲያስተካክል ጠይቋል።

የሰላም ስምምነቱ ባለቤት የሆኑመላው የድርጅቱ አባላት፣ የትግራይ ህዝብና ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይህንን ውሳኔ የሰላም ሂደቱ አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑ ተገንዝበው የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉም ህወሓት ጥሪውን አቅርቧል።

የፌደራል መንግሥትም ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ በተጀመሩት አወንታዊ የሰላም እና የመደጋገፍ ጥረቶች ላይ ሊያሳድረው የሚችል አላስፈላጊ ጫና እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ ህጋዊ ውሳኔዎችንና ስምምነቶች በኹሉም የመንግሥት ተቋማት እና አካላት እንዲከበሩ የማድረግ ሀላፊቱን ግምት ውስጥ በማስገባት የቦርዱን ውሳኔ እንደገና ታይቶ ከህወሓት ህጋዊ ሰውነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች ያሉትን ህጋዊና ፖለቲካዊ አማራጮች ተጠቅሞ ነገሮች ቅድመ-ጦርነት ወደ ነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ በሚያደርግ ቀና አካሄድ እንዲፈቱ፣ የፕሪቶርያ ስምምነት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ እና የተጀመረውን የሰላም ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲያደርግ ጥሪውን አቅርቧል።

በተጨማሪም የፕሪቶርያ ስምምነት እንዲሳካ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት ደግሞ በተለይ ሂደቱ የሚያደናቅፍ እና አደጋ ውስጥ የሚከት የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ፤ በፕሪቶርያ ስምምነት መሰረት ተቃኝቶ እንዲስተካከል የድርሻቸውን እንዲወጡም ህወሓት በመግለጫው ጠይቋል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ጨምሮ በሶስት የትግራይ የፖለቲካ ፖርቲዎች የምዝገባ ሂደት ማስቀጠል እንዲሁም ሕጋዊ ሰውነት መመለስ በተመለከተ የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላልፏል። ቦርዱ ህወሓት ዳግም ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስለት ያቀረበው ጥያቄ ሳይቀበል የቀረ ሲሆን፣ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀስ የሚችለው በድንጋጌው መሰረት ዳግም የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ በሕጉ መሰረት ሲፈቅድ መሆኑ ወስኗል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) በተባሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ ደግሞ በተጠቀሰ አዋጅ መሰረት ዳግም መስራች ጉባኤ ሊያደርጉ ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ ዙርያ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ። ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ ቦርዱ ሕጋዊ ሰውነት ዳግም ለመመለስ የሚያስችለኝ የሕግ አግባብ የለም ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ህወሓትን ለመሰረዝ የሄደበት ሂደት ጭምር የሕግ ክፍተት የነበረበት፣ የምርጫ አዋጅ ያላከበረ እና ሂደቱ ያልጠበቀ ነበር በማለት ይተቻሉ።

ህወሓት የሰላም ስምምነቱ ፈራሚ አንድ አካል ከመሆኑ አንፃር፣ ይህ የቦርዱ ውሳኔ እንዴት ይመለከቱታል ብለን ጥያቄ ያቀረብንላቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ “የህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ አንዱ የጦርነት አካል ነው። ኢትዮጵያውያን ያሳለፍነው ተራ የፍርድቤት ወይ ምርጫ ቦርድ ክርክር አይደለም። ሚልዮኖች አልቀውብን ነው ዕልባት የተገኘወ። [ቦርዱ] ጉዳዮ በውን አላየውም። የሕግ ክርክር ነው ማንሳት የፈለጉት” ያሉ ሲሆን፣ ቦርዱ ጉዳዩ መለስ ብሎ ይመለከተዋል ብለው እንደሚያስቡ ጠቁመዋል።

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከህወሓት በኩል ዝርዝር ማብራርያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም። ሌላው ከቦርዱ ዳግም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ውሳኔ የተሰጠው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ነው። የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ኮምኒኬሽን ሐላፊ አቶ ሃይለአብ ሃይለስላሴ ለዶቼቬለ እንዳሉት የቦርዱ ውሳኔ ስህተት ነው። ኮምኒኬሽን ሐላፊው ጨምረውም ” በዚህ ጉዳይ ዙርያ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ አቋም የቦርዱ ውሳኔ ፍትሓዊ አይደለም ነው። ምክንያቱም እኛ የምዝገባ ሂደታችን ለማጠናቀቅ በትክክለኛ መንገድ ነበር ስንጓዝ የነበረው። ተፈቅዶልን የምዝገባ ሂደታችን በመከወን ላይ የነበርነው በነባሩ የፖርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ነው። አሁን ላይ ቦርዱ የኛ ጉዳይ እየተመለከተ ያለው ግን በአዲሱ የምዝገባ አዋጅ መሰረት ነው” ያሉ ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ጥያቄው ለቦርዱ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ እንዳለ አቶ ሃይለአብ አክለው አንስተዋል።