“ደሜን ባፈሰስኩላት መንበር ላይ ተዝናንተህ በመቀመጥ ዛሬ በኦርቶዶክስ ክርስቲያን ላይ የምትሳለቅ ርክበ ካህናት ሆይ! ወዮልህ ! ተጠንቀቅ! የማትወጣው ዋይታ ከፊትህ እየጠበቀህ ነው! በማለት ሰማዕቱ ፓትርያርክ ቴወፍሎስ ርክበ ካህናቱን እያስጠነቀቁ ናቸው፡፡
ሙሉውን ጽሁፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ።
በቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com
ርክበ ካህናት ምን ማለት ነው? ምንድነው ጥቅሙ? ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ባቀረብኳቸው ጽሑፎቼ እንደገለጽኩት በየአመቱ ዑደታቸውን ጠብቀው ከሚመላለሱት ማኅበራውያት መገናኛዋቻችን (በዐላቶቻችን ) አንዱ ሰሞኑን የሚራገበው ርክበ ካህናት ነው፡፡ በየዐመቱ የምናከብራቸው በዐላቶቻችን ካህናት ሳይቀሩ ጠቅላላ ሕዝቡ ስርወ ታሪካቸውን ለማስታወስ ብቻ ባህልን በመከተል የማናከብራቸው እንደሆነ አድርገው እንደተመለከቱት ተግንዝቤአለሁ፡፡ አቤት ትልቅ ውድቀት !
በዐላቶቻችን ከስረወ ታሪካቸው ማስታወሻነታቸው ባሻገር በአገርና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያንዣበበውን የጥፋት ማእበል ለመከላከልና በደጀንነት ቆሞ ህዝበ ክርስቲያኑን ለመታደግ ነበር፡፡ ፖለቲከኞቹ ነገረ መለኮቱንና ቀኖናውን በመደምሰስ ብቻ ሳይወሰኑ መተርጎም በሚችሉት ሊቃውንት አባቶች ላይ ምን ያህል እንደተዘመተባቸውም ተረዳሁ፡፡ ከስርወ ታሪኩ በመነሳት ከበዐላቶቻችን አንዱ የሆነው ርክበ ካህናት ሕዝባዊ ደጀንነቱንና ተከላካይነቱን ለመግለጽ ከስሙ ትርጉም እጀምራለሁ፡፡
ርክበ ካህናት
ርክብ የሚለው ቃል “ተረክበ” (ተራከበ) ከሚለው ግሥ የወጣ ዘር ነው፡፡ ትርጉሙ የተገኘ ወይም የተገናኘ ማለት ነው፡፡
ካህናት የሚለውም ቃል “ተክህነ” ከሚለው ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጉሙ የሞት ፍዳ ለሚጠይቅ ተልእኮ የተሰለፉ አገልጋዮች ማለት ነው፡፡
ሁለቱም ቃላት ርክበ ካህናት ተብለው አንድ ላይ ተገጣጥመው ሲናበቡ (ሲነበቡ) እስከሞት ለሚያደርስ ተልእኮ የተሰለፉ ብጹአን ቅዱሳን (በዓለም ካሉ ሰወች የተለዩ) ሰወች የተሰለፉበት (የተገናኙበት ስብሰባ”) ማለት ነው፡፡ የስሙ ትርጉም እንደሚያሳየው እስከሞት ለሚያደርስ ተልእኮ መሰለፍ መሆኑን ከተረዳን ማን እንደ ጀመረው መቼና ለምን እንደ ተጀመረ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡
ስረወ ታሪኩን ማን ጀመረው? እንዴት? መቼና ለምን ተጀመረ?
ርክበ ካህናት የተጀመረው ሐዋርያት የሰሩትን ሥራ በሚተርከው መጽሐፍ ምዕራፍ (6) ላይ እንደሚነበበው በሐዋርያት ዘመን ነው፡፡ የተጀመረው በችግር መክንያት ችግር ለመፍታት ነው፡፡ በመጀመሪያወቹ ክርስቲያኖች ህብረት መካከል በአድላዊነት ያስተዳደር መዛባት ተከሰተ፡፡ ያስተዳደሩን መዛባት ማስተካከል የሚያስችል ጥበብ ያላቸው እስጢፋኖስ ያለበት ሰባት ሰወች ወደፊት ለማምጣት ሕብረቱ ተገደደ፡፡ (ምዕ 6 ቁ 6፡)
ወደ ተመረጡለት ሥራ ሲገቡ፡ ከሁሉም በጥበቡ የላቀው እስጢፋኖስ የሚባለው ከተመረጡለት ተግባር ውጭ መሰዋዕትነት የሚጠይቅ ተግዳሮት አስቀድሞ ተመለከተ፡፡ ይህን ተግዳሮት በቅድሚያ ተፋልሞ ካላሰወገደ የተመረጠለት ተልእኮ ዘላቂ ግቡን እንደማይመታ ተረዳ፡፡
የተከሰተው ችግር የውስጥ ያስተዳደር ብልሹነት ብቻ አልነበረም፡፡ ለፖለቲካ ዘላቂ የነጻነት መፍትሄ እንፈልጋለን የሚሉ ሰወች “ሊቤርጥኖን” የሚል ስም ለድርጅታቸው ሰጥተው በቤተ ምኩራብ እየተሰበሰቡ እንታገላለን የሚሉ ሰወች ነበሩ፡፡ መጀመሪያ መፍትሔ እንፈልጋለን በሚሉ በራሰቸው በፖለቲከኞች የተጠነሰሰው ትብትብ ካልፈረሰ ያስተዳደሩ ብልሹነት እንደማይሳካ የተረዳው እስጥፋኖስ ፖለቲከኞቹ (ሊቤርጥኖናያውያኑ) ወደተሰበሰቡት ምኩራብ ሳይጋበዝ ሰብሮ ገባ ፡፡ (የሐዋ 6፡9)፡፡
ሕዝቡን ነጻ ሊወያጡ ይቅርና ካባቶቻቸው ከወረሱት ከግብዝነት ሕገወጥነትና ያልተላቀቁ፤ በሞራልና በታማኝነት ህሊናቸውን ያልገረዙ ሆነው እስጢፋኖስ አገኛቸው፡፡“እናንት አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሯች ሁ ያልተገረዘ፤ ተቀብለናል የምትሉትን የመላእክትን ሕግ እንኳን የማትከትሉ፤ የመነፈስ ቅደስ ተቃዋሚወች ያባቶቻችሁን የነፍሰ ገዳይነት ታሪክና ግብር የምትከትሉ” (የሐዋ ምዕ 7፡51_53) እያለ ሞራለ ብልሹነታቸውን በሙሉ ልብ ነገራቸው፡፡
ከስር ጀምሮ ታሪካቸውን ተንትኖ በመናገር የራሳቸውን ክፋት ተንኮልና ሸረኝነት እውነትን ከሀሳት ጋር በሚያቀራርብ አርስጣጣላዊ ጽሑፍ ሳያጠይም ነገራቸው፡፡ ነርቫቸው ተናወጠ፡፡ ጥርሳቸው እስኪፋጭ ድረስ ቁጣቸው በሱ ላይ ነደደ (7፡54)፡፡ መስማት ባይፈልጉም ጆሯቸውን ደፍነው በታላቅ ድምጽ እንዲጮኹ አስገደዳቸው፡፡
በሸፍጠኝነት የተደፈነውን ጆሯቸውን ሰንጥቆ በጭንቅላታቸው ገብቶ ያስጮኸቸውን ተግሳጽ ለማፈን የሀሰት ምስክሮችን (ካድሬወቻቸውን) አሰሰለፉበት (6፡ 14) ፡፡ እውነት የምትጠይቀውን የሞትን ግዳጅ ፈጸሙበት፡፡ የሞት ተልእኮውን ሲፈጽም የተልኮው ባለቤት የሆነው የካህናት አለቃ ጌታችን ከመለኮታዊ ዙፋኑ ተንስቶ በመቆም ተቀበለው፡፡
“የማእድን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የግዚአብሔርን አገልግሎት መተው አይገባንም” ብለው ለትልቁ አገልግሎት ራሳቸውን ሰይመው የነበሩት ሐዋርያት የችግሩን ምንጭ መመልከት ተሳናቸው፡፡ በተቃርኒያቸው ለዝቅተኛው አገልግሎት ያሰለፉት እስጢፋኖስ ታላቁንና መስዋዕትነት የሚጠይቀውን ተልእኮ በመፈጸም ቀደማቸው፡፡ (2)
በዚሁ መጽሐፍ ምዕ 15 ላይ እንደተመዘገበው ከእስጢፋኖስ በኋልም ሐዋርያት የእስጢፋኖስን ምሳሌነት በመከተል በቅድሚያ ሊደረግ የሚገባውን ቀድመው በማየት እንደ እስጢፋኖስ ተመሳሳይ ተልእኮ ፈጸሙ፡፡ “ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶች ተንስተው የሙሴን ሕግ በመጠበቅ ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም” የሚል ሐሳብ አንስተው በርክበ ካህናታቸው እንዲወስኑ ሐዋርያትን ጠየቋቸው፡፡ (5) ፡፡
በርናባስም ጳውሎስም የየራስቻውን ሀሳብ አፈለቁ (12) የእስጢፋኖስን ምሳሌነት የተከተለው አርቆ ተመላክቹ ያዕቆብ “ግርዘትን የመሳሰሉትንማ ስንሰብክ ኖረናል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ግርዘትን በመሳሰሉ ተራ ነገሮች ላይ በማተኮር ጊዜያችንን አናባክንም፡፡ አሁን ፋታ የማይሰጡ በህዝባችን ላይ የሕይወት አደጋ ያንዣበቡ ለጣዖት የተሰዋ ነገር በመብላት፤ ደም በመጠጣት፤ ታንቆ የሞተ የእንስሳ ሥጋ በመብላትና በዝሙት የሚመጡ ርኩሰቶች” ያስከተሏቸው ሕዝባውያን እልቂቶች ከፊታችን ተጋርጠዋልና እናንተ ያቀረባችኋቸውን የመነጋገሪያ ሀሳቦችን አንቀበልም ብሎ የሐዋርያት ሲኖዶስ ወረወረው ፡፡ (29)
አንባቢና አድማጭ ሆይ ተመልከት! ተሰብስበው እንዲወስኑ ባስመሳዮች ፈሪሳውያን ሐዋርያት የተጠየቁት ስለ ግርዛት ነበር፡፡ ሆኖም ፈሪሳውያን ከሚያውቁት ግርዛት ይልቅ የሐዋርያት ሲኖዶስ የበለጠ በህዝብ ላይ ከፍተኛ እልቂት የሚያስከትሉ ተግዳሮቶች እንዳሉ ተምለከተ፡ ርክበ ካህናቱ ከተነጋገረባቸው በኋላ “እኛና መውንፈስ ቅዱስ ወስነናል” ብሎ የፈሪሳውያንን አወናባጅ ትብትብ በጣጥሶ እንደ መርገም ጨርቅ ወረወረው ፡፡
ርክበ ካህናቱ በፈሪሳውያን ሐሳብ ሳይወናበድ ወደ እውነት ወደ ፍትሕና ወደ ጽድቅ በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የወሰነውን ውሳኔ ከቃኘ በኋል ተመልካቹንና ሰሚውን ሁሉ በነገረ መለኮቱና በቀኖናው ቁጥጥር እንዳደረገው ተገነዘበና “ልብን የሚአውቅ አምላክ ለኛ የመወሰን የመመርመር ጥበብ እንደሰጠን ለነሱም ስለሰጠ ልባቸውን በእምነት አዘጋጅቶ በኛና በነሱ መካከል የሀሳብ ልዩነት አልነበረም” አለ (8 ) ፡፡
ለርክበ ካህናት ተልእኮ የመጀመሪያ ምሳሌወቻችን አስጢፋኖስና ሐዋርያት ሲሆኑ፤ በየዘመናቱ የተነሱ በዘምናቸው የተከሰቱትን ሕዝባውያት አደጋወች ለሕይወታቸው በመጓጓት ከሚገጥማቸው አደጋ ሳያፈገፍጉ እንደ እስጢፋኖስና እንደ ሐዋርያት ህዝባቸውን ያተረፉ ብዙ የምንጠቅሳቸው ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አሉን፡፡ በዘመናት ርቀት ባይናችን ባንያቸውና በእጃቸው ባንዳሰስም የተጻፈላቸውን ታሪክ በመማር በቃላቸው ተዳሰናል፡፡
ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴና ቀዳማዊ ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እንደ መምህር ገ/ ኢየሱስ መሆን ይችላሉ ተብለው ተምረው በደብረ ሊባኖስ ገዳም በስማቸው በተከፈተው ት/ቤት ገብቼ ተምሬ ነበር፡፡ ምሳሌያቸውን ተከትየ እንደ እሳቸው ወገንን ለመታደግ የሰማእትነት መስዋዕት ለመሆን ባልታደልም የምናገረው ምስክርነት ለህዝቡ እንዳይደርስ በዘመኑ ካህናት ጫጫታ መታፈኔ እጅግ ያሳዝነኛል፡፡
ባለመታደሌ ሊቅነትን ብህትውናንና ሰማእትነትን አጣምረው የመታደግን ተልእኮ በመስዋእትነት እንደ ገለጹት እንደ መምህር ገ/ ኢየሱስ ለመሆን ባልበቃም ፡፡ በትምህርት ቤት ቆይታየ ከሳቸው ጋራ ያሰለፍኩት ንክኪ አላስቆም አላስቀመጥ አላስተኛ ብሎ ስለሚያስለፈልፈኝ በዘመኑ ካህናት ለፍላፊ የሚል ቅጽል አሰጥቶኛል፡፡
ሁለተኛው በዐይኔ ያየኋቸው በቃላቸው የተመከርኩባቸውና በጃቸው የተዳሰስኩባቸው ሰማእቱ ፓትርያርካችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴወፍሎስ ናቸው፡፡ ሰማእቱ ፓትርያርካችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ቴወፍሎስ ቤተ ክርሲቲያናቸውን ነቃቅሎ ለመጣል በኮምኒስቱ ያንዣበበውን መከራ እንደ እስጥፋኖስና እንደ ያዕቆብ ከሁሉም አስቀድመው ተመለከቱ፡፡ በንብረትና በመሬት ይዞታ አሳቦ ብዙ ሕይወት ያጠፋውን የኮምኒስቱን አደገኛነት ባካባቢያቸው ከነበሩት ጳጳሳት፡ ከደብር አለቆችና ከገዳማት አበምኔቶች ሁሉ ቀድመው ተረዱ፡፡
ኮምኒስቱ መሬት ላራሹ በሚለው መርሆ ከመሳፍንቱ ስርአት ጋራ ንክኪ የነበራቸውን ተቋማት እያራከሰ ሲያፈራርስ ሰወችንም ሲገድል፡ አቡነ ቴወፍሎስ ያንዣበበውን ጥፋት አስቀድመው በማየት በቃለ ዓዋዲው አዋጃቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ከመሳፍንቱ ስራቱ ነጻ በማድረጋቸው የኮምንስቱ ስርአት በቀድስት ቤተ ክርስቲያናቸው ላይ እንከን እንዳያገኝባት አድርገዋል፡፡
ቃኤልን ተጠናውቶ የራሱን ወንድም ያስገደለው ሰይጣን ዛሬ የተጠናውታቸው ኢትዮጵያውያን ከ 50 አመት በፊት አቡነ ቴወፍሎስ ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያስወገዱትን እንከን ብልጽኛወች ራሳቸው ያስወገዱ በማስመሰል የሐሰት ትርክት በመናገር ቤተ ክርስቲያናችንን እየከሰሱ ነዋየ ቅድሳቷን እያቃጠሉ፡፡ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን በአራት ምክንያቶች እያሰደዱ በመግደል ላይ ናቸው፡፡
1ኛ፦በኦርቶዶክስ እምነታቸው፡፡
2ኛ በኢትዮጵያዊነታቸው
3ኝ በአማራነታቸው
4ኛ በአማርኛ ቋንቋ ተናጋርነታቸው እያደኑ ከኢትዮጵያ ገጸ ምድር እያጠፏቸው ናቸው፡፡ በእስጢፋኖስ ዘመን “ሊቤርጥኖን” በሚል ስም እንደነበረው ማለትም ለነጻነት እንታገላለን የሚሉ ብልጽግናወች ወደ ሚሰበሰቡባት ምኩራብ ገብቶ የሚፋለም አንድ ሰው እንኳ ጠፋ፡፡
በኢትዮጵያ ላይ የዘመቱት “ሊቤርጥኖናውያን” ኢትዮጵያን የገዳይና የተገዳይ፤ የአፈናቃይና የተፈናቃይ፡ የተሰዳጅና ያሳዳጅ፡ የቀባሪና የተቀባሪ፡ ያልቃሽና ያስለቃሽ ከተማ አድርገዋታል፡፡ እየጨፈጨፉ የሚገሉት የሰው ሥጋና አጽም ገጸምድሯን ሸፍኖታል፡፡ አፈሩ በሰው ደም ጨቅይቷል፡፡ የሚነፍሰው አፈር ትቢያ የሆነውን የወገንን ሥጋ ባፍንጫችን እየጋተን ነው፡፡ የምንጠጣው በወገኖቻችን ደም የተቀላቀለ ውሀ ነው፡፡ ነፋስ ከመሬት እየጠረገ በሰውነታችን ላይ የሚበትነው ትቢያ ሰወነታችንን እያለበሰው ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ሁላችንም ሙታን በመሆናችን ስርአተ ቀብር የሚፈጽም ቄስ የለም፡፡ አልቅሶ ገንዞ የሚቀብር ወገንም የለም፡፡ አፈር ትቢያ ሆኖ ነፋስ በላያችን በሚበትነው በወገን አካል እየተቀበርን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን አናት ላይ የተሰበሰበው ርክበ ካህናት ለመነጋገሪያ ያዘጋጀውን ሰነድ ስመለከተው በእስጢፋኖስ ዘመን ከነበሩት ሊቤርጥኖናውያን ሰነድ እጅግ የከፋ ሆኖ አገኝሁት፡፡ለሐዋርያት ፈሪሳውያን ያቀረቡላቸው ሰነድ በእጅጉ ተሽሎ አገኘሁት፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸው ተደራራቢ መከራና እልቂት የተነጣጥሩት አራቱን ሁሉ ሰብስቦ በተገኘው በአማራው ላይ ቢሆኑም፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ባንዱ ወይም በሁለቱ ንክኪወቹ ከተነጣጠረው እልቂቱ አላመለጡም፡፡
እልቂቱ ከሚፈጽሙት ፖለቲከኞች መካከል ገብቶ “እናንት አንገተ ደንዳኖች ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ የመነፈስ ቅደሱ ተቃዋሚወች ያባቶቻችሁን ነፍሰ ገዳይነት የምትከትሉ በመላእክት ሥርአት ሕግን ተቀብላችሁ ያልጠበቃችሁት እናንተም እርሱን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ገደላችሁትም”(7፡51_53) እያለ በሙሉ ልብ እንደ እስጢፋኖስ የሚፋለም ከጳጳስቱ አንድ ሰው አልተገኘም፡፡
በሐዋርያት ዘመን የነበሩት ወደ ተመረጡለት ሥራ ሲገቡ፡ ከሁሉም በጥበቡ የላቀው እስጢፋኖስ የሚባለው ከተመረጡለት ተግባር ውጭ መሰዋዕትነት የሚጠይቅ ተግዳሮት አስቀድሞ የተመለከተ ጠፋ፡፡ ይህን ተግዳሮት በቅድሚያ ተፋልሞ ካላሰወገደ የተመረጠለት ተልእኮ ዘላቂ ግቡን እንደማይመታ የተረዳ ጳጳስም አልተገኘም፡፡
ርክበ ካህናት በኢትዮጵያ ላይ የተከሰቱትን ከላይ የተዘረዘሩትን ሁሉ ግፎች መከራወች እየደረደረ በመግለጽ ሊበርጥንያኖችን በሙሉ ልብ መፋለም ሲገባው ከሊበርጥንያኖች ጋራ እየተስማማ አርስጣጣላዊ (እውነትን ከሐሰት ጋራ የቀላቀለ ) ደብዳቤ ለብልጽግናወች (ሊበርጥንያኖች) በማቅረብ ሕዝቡን እያስገደለ ነው፡፡
ፈሪሳውያን ካቀረቡላቸው ከግርዘቱ ይልቅ ጊዜና ፋታ የማይሰጥ የከፋ ነገር በሕዝቡ ላይ ያንዣበበ አደጋ ለሐዋርያት የታያቸው “በጣዖት በዝሙት የታነቀ በመብላትና የእንስሣት ደም በመጠጣት” የሚያስከትለው አደጋ ነበር፡፡ ሐዋርያት ፈሪሳውያን ባነሱት ጥያቄ ሳይወናበዱ ትኩረታቸውን ከግርዛት አንስተው “በጣዖት በዝሙት ወድቆ የተገኘ ሥጋ በመብላትና የእንስሣት ደም በመጠጣት” በሕዝብ ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ሕዝቡ ተረድቶ እንዲርቅ በውሳኔያቸው አስጠነቀቁ፡፡
የዘመናችን ርክበካህናት የተግዳሮት ሁሉ ምንጭ የሆነውን የፖለቲካ ቡድን በቅድሚያ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ መስዋዕት እስኪሆን ድረስ ባለመፋለሙ፡ እንደ ሐዋርያትም ከብልጽግና ጣዖትነት ርቆ የተገኘውን ሁሉ ከመካፈልና ከዝሙቱም ራሱን ባለመጠበቁ የተሰለፈለት ተልእኮ ዘላቂ ግቡን እንዳይመታ አድርጎታል፡፡ በተቃራኒው ቡድኑ ባቀረበለት አቅጣጫ አሳሳችና አዘናጊ የመነጋገሪያ ሸለቆ ውስጥ ገብቶ ተቀርቅሯል፡፡
ሰማእቱ አቡነ ቴወፍሎስ በሕይወት መስዋዕትነታቸው ከ50 አመት በፊት እንከን አልባ ያደረጓትን ቤተ ክርስቲያን መግሥት በሐሰት ትርክቱ ከኮምንሲቱ በፊት ወደነበረው መሳፍንታዊ ስርአት መልሶ በመክተት የቤተ ክርስቲያንን ነዋየ ቅድሳት እያቃጠለ ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑንም እየጨፈጨፈ ነው፡፡
አቡነ ቴወፍሎስ ደሜን ባፈሰስኩላት መንበር ላይ ተዝናንተህ በመቀመጥ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝበ ክርስቲያኑን ከሚጨፈጭፈው ጋራ ተስማምተህ የምትሳለቅ ርክበ ካህናት ሆይ! ዋልህ ! የማትወጣው ዋይታ ከፊትህ እየጠበቀህ ነው! በማለት ርክበ ካህናቱን እያስጠነቀቁ ናቸው፡፡
ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓም. (ሜይ 17, 2023)
