ከውጭ የልማት አጋሮች ዘንድሮ ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 7.7 ቢሊዮን ብር፤ እስካሁን “ፈሰስ አለመደረጉን” የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ
የፌደራል መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥታ የበጀት ድጋፍ 7.7 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ቢያቅድም፤ እስካሁን “ፈሰስ አለመደረጉን” የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሶስት ሚሊዮን ዜጎች በጦርነት እና ግጭት ሳቢያ “ወደ ከፋ ድህነት” መግባታቸውን በጥናት ማረጋገጡንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይህን ያስታወቀው የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፤ ለተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 9፤ 2015 ባቀረበበት ወቅት ነው። በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በቀረበው የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የመንግስትን ገቢ የሚመለከተው ይገኝበታል።
የፌደራል መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት፤ ከታክስ፣ ታክስ ካልሆኑ እና ከውጭ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ 446.5 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ እንደነበር በሚኒስቴሩ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የታክስ ገቢ ሲሆን፤ ከዚህም 400.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር። በዘንድሮው በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በተያዘው በዚህ እቅድ፤ “ከውጭ የልማት አጋሮች የሚመጣ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ” በሚል ታሳቢ ተደርጎ የነበረው 7.7 ቢሊዮን ብር ነበር።
