ሀገራችን ኢትዮጵያ እየተመራችበት የምትገኘው ህገ መንግሥት ለአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ በደል ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ሆኖም ሀገራችን በዚህ ህገ-መንግሥት የምትመራበትን ዘመን የአማራ ሕዝብም በትግሉ እንዲያበቃ እስከሚያደርግ ድረስ ደግሞ በዚህ ህገ-መንግሥት መመራት ግድ እንደሆነ እናውቃለን።
በህገ-መንግሥቱ በምንመራበት ሁኔታ ደግሞ ህገ-መንግሥቱ በሰጣቸው መብቶች የክልላችን ሕዝብ እና መንግሥት ተጠቃሚ መሆን አለበት። በዚህ መሰረት የሀገሪቱ ክልላዊ መንግሥታት የራሳቸው ሉአላዊ ስልጣን ያላቸው መሆኑን የሚዘረዝርባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የክልሎች መንግሥታት እርዳታ እስካልጠየቁ ድረስ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በክልሎቹ ዘው ብሎ ገብቶ የክልሎቹን ሕዝብ ማሸበር፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ መተኮስ እና መፍጀት፣ የጅምላ እስርን በጠመንጃ አስገዳጅነት ማሳለጥ እንደማይችል መደንገጉ ነው።
ይህ የመከላከያ ሰራዊት በክልሎች እንደፈለገ ገብቶ የማተራመስ ተግባር ኢ-ህገመንግሥታዊ በመሆኑ ከአማራ ክልል በቀር በሌሎች የሀገራችን ክልሎች (አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በተከሰቱባቸው እንደ ወለጋ፣ የአሁኑ የሲዳማ ክልል ሳይቀር) ይሄው መከላከያ ሰራዊት “አልታዘዝኩም” በሚል ሰበብ የንጹሀንን ህይወት ለመታደግ እንኳን በሰላማዊው የአማራ ክልል የፈጠነውን ያክል ፈጥኖ አልገባም።
በአሁኑ ወቅት የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልል ገብቶ እየፈጸመ ያለው አስነዋሪ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ሳይሆን የኦሮሞ ብልጽግና-መራሹ ፓርቲ የግል ንብረት ለመሆኑ ግልጽ ማሳያ ነው። በአጠቃላይ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በኦሮሞ ጄኔራሎች የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት የኦሮሞ ብልጽግና-መራሹ አገዛዝ ኦነጋዊ ተልዕኮ አስፈጻሚ ለመሆኑ ዋናው ማሳያ በወለጋ ለአራት አመታት ያክል የዘለቀውን የንጹሀን አማሮች እልቂት ለማስቆም አንዳችም ጥረት ያላደረገ መሆኑ ነው።
ስለዚህ ጉዳይ ላይ ኢሳት ከተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲቀርብለት የመከላከያ ሰራዊትን የሚመራው ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “ወለጋ ገብተን የአማሮችን ህይወት ያልታደግነው የፌደራሉ መንግሥት ስላላዘዘን ነው” ሲል መልሷል። ይህ ሰው የሚናገረውን እንደሞኝ ሰው ሆነን እንመን ከተባለ የፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሰራዊትን ወደ አንድ ክልል ገብቶ የንጹሀንን ህይወት እንዲታደግ የሚያዘው ክልሉ የመከላከያን እርዳታ በፌዴራል መንግሥት በኩል ሲጠይቅ ነው። እንደ ወለጋ ባለ መፈጠርን በሚያስረግም በአማራ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለ ዘር-ተኮር ጭፍጨፋ እና የጅምላ ፍጅት ሲኖር ደግሞ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ደርሶ የንጹሀንን ህይወት እንዲታደግ የሚያዝበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም። ኦሮሞ-መራሹ የፌደራል መንግሥት ይህን በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ፍጅት እንዲቆም ያላደረገው “ሸኔ” እያለ ከሚጠራው አረመኔ ቡድን ጋር የተለየ አቋም ስለሌለው ብቻ ነው።
የሆነው ሆኖ በወለጋ ለዓመታት የዘለቀውን የንጹሀን አማሮች እልቂት ለመታደግ “ስላልተጋበዝኩ አልገባሁም” የሚለው የኦሮሞ-መራሹ መከላከያ ሰራዊት በአሁን ሰአት ፍጹም ሰላማዊ ወደሆነው የአማራ ክልል በገፍ እየገባ ንጹሃንን የሚገድለው፣ የጅምላ እስሩን በአጋፋሪነት የሚመራው፣ ሰላማዊውን ሕዝብ የሚያሸብረው ማን ጋብዞት እንደሆነ በአስቸኳይ ግልጽ ሊያደርግ ይገባል። የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ያለውን አቋም በይፋ ግልጽ ማድረግ አለበት።
የአማራ ክልል ብልጽግና መንግሥት በኦሮሞ ጄኔራሎች የሚዘወረውን የመከላከያ ሰራዊት ወደ አማራ ክልል ገብቶ እየሰራ ያለውን ስራ እንዲሰራ ፈቅዶ ከሆነ የአማራ ተወላጆች በየቀኑ በጅምላ ከሚያልቁበት የኦሮሚያ ክልል ከገጠመው ችግር የበለጠ ገጥሞኛል እያለ እንደሆነ የአማራ ሕዝብ እንዲገነዘብ ማስታወስ እንወዳለን።
በአጠቃላይ በኦሮሞ ጄኔራሎች የሚዘወረው የመከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ገብቶ እያደረገ ያለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶ የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልላዊ መንግሥት በአስቸኳይ ማብራሪያ እንዲሰጡበት የአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ በጥብቅ ያሳስባል። የሚሰጠው ማብራሪያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በክልሉ እንዲገባ ከማያስፈልጉ ህገ-መንግሥታዊ ቅድመ-ሁኔታዎች አንፃር ሊቃኝ እንደሚገባ ለማስታወስ እንወዳለን። ካልሆነ ግን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተግባራዊ ስራው ኦነጋዊ አማራ-ጠል አላማ ማስፈጸሚያ ተቋም መሆኑን ለአማራ ሕዝብ ግልጽ ማድረግ እንወዳለን።
ይህ የመከላከያ ሰራዊት በኦነግ ጄኔራሎች እየተመራ ለአማራ ሕዝብ ከሞት እና ዋይታ በስተቀር ሊያመጣ የሚችለው አንዳች በረከት እንደማይኖርም የታወቀ ሀቅ ነው። ስለሆነም የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥታት የመከላከያ ሰራዊትን በገፍ ወደ አማራ ክልል አጓጉዘው የሚሰሩትን ኢ-ህገመንግሥታዊ ተግባር እስካላቆሙ ድረስ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያሉ የአማራ ተወላጅ የጦር መኮንኖች እና እግረኛ ወታደሮች በገዛ ሕዝባቸው ላይ ጭፍጨፋ ለመፈጸም ከኦነጋዊው ስርዓት ጋር እየተባበሩ እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል። ሕዝባቸውን አምርሮ ከሚጠላው ኦነጋዊው ስርዓት ጋር መተባበርን ካልፈቀዱ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከአማራ ክልል ለቆ እንዲወጣ የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ የአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ ጥሪ ያቀርባል።
የአማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!
ህልውናችን በክንዳችን!
የአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ
