May 19, 2023 – Getachew Shiferaw

ሲኖዶሱ ሰሞኑን ስብሰባ ላይ ሲሆን እነ ሽመልስ አብዲሳ፣ ብርሃኑ ጁላ፣ደመላሽ ወልደሚካኤልን ጨምሮ በቀጥታ ጫና በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ አመራሮች “ባሉት ቦታዎች ኦሮሞ ካልሾማችሁ የኦሮሞ ሲኖዶስ እንዲቀጥል ይደረጋል።” በሚል ጫና እያደረጉ ነው። የተጠቀሱትን ጨምሮ በፌደራልና ክልል አመራርነት ላይ ያሉ የኦሮሚያ ብልፅግና አመራሮች ዋና ስራቸው ሲኖዶስ ላይ ማሾም ሆኖ ሰንብቷል።

የሲኖዶሱ አባላት በመንፈስ ቅዱስ እንጅ በትዕዛዝ ሹመት እንደማይሰጥ ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን የኦህዴድ ወታደራዊ፣ የመከላከያና የፀጥታ አመራሮች ግን እንደ ወረዳና ዞር አመራር ምደባ ለቤተ ክርስቲያንም እኛው ነው የምንሾመው ብለዋል። ካሉት 24 ቦታዎች በሙሉ የተወገዘውውን ቡድን አባላት እንዲሾሙም የሲኖዶሱ አባላት ጫና እየተደረገባቸው ነው።

የኦሮሚያ ብልፅግና ኦርቶዶክስ መፈንቅለ መንግስት ልታደርግብን ነው ሲል የከረመ ሲሆን በጠላትነት የፈረጃትን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው ተብሏል። ኦሮሚያ ውስጥ የተወገዘው ቡድን አባላት በእነ ሽመልስ አብዲሳ ፍላጎት በየደብሩ በስራ ከአስኪያጅነት ጀምሮ እየተመደቡ ሲሆን ጥበቃ የሚያደርጋቸውና በክልሉ ፀጥታ ኃይል ነው። በአንፃሩ ሲኖዶሱ የሾማቸው አባቶች ኦሮሚያ ውስጥ አሁንም እየተሳደዱ ነው።

የኦሮሚያ ብልፅግና ስልጣኑን ለማስቀጠል የትርክ ለውጥ ማድረግ አለብኝ የሚል አቋም የያዘ ሲሆን ለኢትዮጵያ አንድነት እና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ቀናኢ የሆነች፣ የኢትዮጵያን ነገስታት የምታከብር፣ የኦሮሚያ ብሌፅግና የሚያፈናቅላቸውን ዜጎች መጠለያ የምትሰጥን ቤተ ክርስቲያን ጠላታችን ነች ብለው ከፈረጇት ቆይተዋል። ቀደም ሲል እነ ሀጅ ሙፍቲንም በሚፈልጓቸው ሰዎች ተክተው መፈንቅለ መጅሊስ ካደረጉ በኋላ “ሸገር ሲቲ” ብለው በጀመሩት ፕሮጀክት 13 መስጊድ ሲያፈርሱ ተቃውሞ አልደረሰባቸውም። በመጂሊሱ ላይ ያደረጉትን ሲኖዶሱ ላይ መድገም የፈለጉት የኦሮሚያ አመራሮች አባቶችን እያገኙም፣ መልዕክት እየላኩ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ነው። እነ ሽመልስና ብርሃኑ ጁላ ኃይማኖታዊ አሰራሩን ጥሰው ሲኖዶሱ እንዲመድብላቸው የሚጠይቁት የሌላ እምነት ተከታይ ሆነው “የኦሮሚያና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” በሚል ለፖለቲካ አላማ ያደራጇቸውን ግለሰቦች ነው።