በቦረና ዞን፣ በቅርቡ ዝናም መጣል መጀመሩን ተከትሎ ሲደረግላቸው የነበረው ሰብአዊ ድጋፍ መቋረጡን የገለጹ የድርቅ ተፈናቃዮች፣ አሁንም ያሉበት አኗኗር ከችግር የማያወጣቸው በመኾኑ፣ ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥባቸው ጠየቁ፡፡
ዱብሉቅ በተባለው የመጠለያ ማዕከል የሚገኙት ተፈናቃዮቹ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግላቸው የሰነበተው ሰብአዊ ድጋፍ፣ ብዙዎችን ከሞት መታደጉን ጠቅሰው፣ ነገር ግን፣ በቅርቡ የዝናሙን መጣል ተከትሎ፣ የድጋፍ መጠኑ መቀነሱን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
የቦረና ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት፣ አሁንም በዞኑ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የምግብ ርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን አስታውቆ፣ ወደፊት ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት የሚቋቋሙበትን መንገድ ለማበጀት፣ ዐዲስ ዕቅድ አውጥቶ ለክልሉ መንግሥት ማስረከቡንና ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደኾነ አመልክቷል።
ከዱብሉቅ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የመጠለያ ማዕከል፣ በቦረና ዞን ትልቁ የድርቅ ተፈናቃዮች መንደር ነው። የወረዳው አስተዳደር ሓላፊዎች ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በዱብሉቅ ወረዳ ብቻ፣ ከስምንት ሺሕ በላይ አባወራዎች ይገኛሉ። የሰባት ልጆች እናት የኾነችው ወይዘሮ ጅሎ ጉራቻ፣ በዚኽ መንደር መኖር ከጀመረች ሁለት ዓመታትን አሳልፋለች።
መጣል ከጀመረው ዝናም የምናገኘው ውኃ ነው፡፡ በዚኽ ፍጥነት መፍትሔ የሚያመጣልን ሌላ ምን አለ? እኛ አርብቶ አደሮች አደሮች ነን፡፡ የነበረችንን አነስተኛ የእርሻ መሬት ትተን ኮብልለናል። ከተረጂነት የሚያላቅቀን ዝናም አሁን መጣል ቢጀምርም፣ ምንም ሳንሠራበት አለፈን፡፡ በፊት ሲደረግልን የነበረው ድጋፍም ተቋርጧል፡፡ በመጠለያው የሚኖሩት ተፈናቃዮች፣ የምንበላው የለንም፤ እያሉ በጣም ሲጨነቁ አያለኹ፤ አሁን ያለው ኑሮ አስከፊ ኾኗል።
በቦረና ዝናሙ ቢጀምርም ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ የድርቅ ተፈናቃዮች ጠየቁ
By ቪኦኤ
