May 19, 2023 – BBC Amharic 

ስንዴ

19 ግንቦት 2023, 12:25 EAT

ዩክሬን በሚሊዮን ቶኖች የሚገመት ስንዴ በጥቁር ባሕር በኩል እንድትልክ የሚፈቅደው ስምምነት ለሁለት ወራት ተራዘመ።

ሩሲያ ስምምነቱን ለተጨማሪ ሁለት ወራት እንድታራዝም የተደረሰውን ስምምነት ያሳለጡት የተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ናቸው።

ከዚህ ቀደም የነበረው ስምምነት ቀነ ገደቡ ሊያልቅ አንድ ቀን ሲቀረው ነው ለማራዘም የተወሰነው።

ሩሲያ ስምምነቱን አታራዝምም የሚል ስጋት ነበር።

የዩክሬን ጦርነት ሲነሳ የምግብ እጥረት ይፈጠራል የሚል ስጋት ነበር። ዩክሩን ስንዴ እና ሌሎችም የእህል ዘሮች በጥቁር ባሕር በኩል እንድትልክ ስምምነት የተፈረመውም ለዚህ ነው።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በተደጋጋሚ ስምምነቱ ታድሷል።

ሩሲያ የግብርና ዘርፏ ላይ በምዕራባውያን የተጣሉ ማዕቀቦችን በተደጋጋሚ ስትነቅፍ ቆይታለች። በዚህም ምክንያት ስምምነቱን ላታድስ ትችላች ተብሎ ተሰግቶ ነበር።

ዩክሬን ከዓለም ግንባር ቀደም ስንዴ አምራቾች አንዷ ናት።

ለአፍሪካ አገራት የደረሰው የዩክሬን እህል

ከስምምነቱ አስቀድሞ ዩክሬን በጦርነቱ ሳቢያ በጥቁር ባሕር እህል ለመላክ አልቻለችም ነበር።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን “በአገራችን ጥረት፣ በሩሲያውያን ወዳጆቻችን ድጋፍ እንዲሁም በዩክሬናውያን ጓደኞቻችን እገዛ አማካይነት የጥቁር ባሕር የስንዴ ስምምነት ለሁለት ተጨማሪ ወራት ተራዝሟል ” ብለዋል።

በዚህ ስምምነት አማካይነት 30 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከዩክሬን ኤክስፖርት ተደርጓል።

ስንዴው በአብዛኛው የሚጓዘው ወደ ባለጸጋ አገራት ሲሆን የታዳጊ አገራት ድርሻ በጣሙን ዝቅተኛ ነው።

ሩሲያ እህል እንዲሁም ማዳበሪያ በብዛት ኤክስፖርት የማድረግ ፍላጎት ቢኖራትም በማዕቀቦች ምክንያት እንዳልቻለች ትገልጻለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ አምባሳደረ ቫሲሊ ኔቤንዚያ “አሁንም ቢሆን ችግሮቻችን ይቀረፋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ያለፈው ጥቅምት ላይ ሩሲያ ለተወሰነ ጊዜ ከስምምነቱ ራሷን አግልላ ነበር።

ዩክሬን በክሬሚያ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን እንደምክንያት ጠቅሳ ሩሲያ ለቀናት ከስምምነቱ ብትወጣም ኋላ ላይ ተመልሳለች።

ከዩክሬን የተላከ የምግብ ምርት