በውጭ ሀገር ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀረበ ጥሪ
በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት ይታያል፡፡ ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት መፍታትና ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ በመሆኑ፣ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ በሂደትም የመተማመንን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት እንዲቻል ገለልተኛ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሟል፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ የዝግጅትና ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን፣ የልየታ መስፈርት እና የአመራረጥ ሂደት መመሪያዎች ዝግጅትን አጠናቆ ወደ ሂደት ምዕራፍ የተሸጋገረበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ስለሆነም በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅማችሁ በሀገራችን የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንድትሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ በቅርቡ በውጭ ሀገራት ከምትኖሩ ኢትጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር የበይነ መረብ ስብሰባ ለማድረግ ያቀደ መሆኑን አየገለፀ የስብሰባውን ቀንና ሰዓት (በየምትኖሩበት ሀገር ሰዓት አቆጣጠር) በዝርዝር በቅርብ የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

