May 20, 2023 – Konjit Sitotaw

” አዲስ ተሽከርካሪዎች ገበያ ላይ የሚሸጡበት ዋጋ እና የሚቆርጡት ደረሰኝ ሰፊ ልዩነት እንዳለው በጥናት አረጋግጠናል ” – የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጠን ጋር በመሆን በተሽከርካሪዎች ግብይትና አሰራር ዙሪያ ትላንት መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

በመግለጫው የተሽከርካሪዎች ግብይት መሬት ላይ ያለው እውነታንና መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ መሠረት ያደረገ ጥናት ሲካሄድ መሠንበቱን ገልጿል።

በዚህም መነሻ ከአስመጪዎችና ከዘርፉ ተሳታፊዎች ጋር ውይይት መደረጉንና ማንም በገበያ ዋጋ ደረሰኝ እንዲቆርጥና ገዢውም ትክክለኛ ደረሰኝ በመያዝ አገልግሎት ማግኘት እንዳለበት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አሳስቧል።

” መንግስት ማግኘት የሚገባውን ገቢ ለማግኘት ከግንቦት 03/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ  ወደ ተግባር ገብቷል ” ያለው የአ/አ ገቢዎች ቢሮ ” የህግ ማስከበር ስራዎች ተጠናክረው ስለሚቀጥሉ ገዢ ላወጣው ለከፈለበት ትክክለኛ ደረሰኝ መቀበል ፣ እንዲሁም ሻጭ ለሸጠበት ትክክለኛ ደረሰኝ መስጠት ይኖርበታል ፤ ሲጠየቁም ይህንን ትክክለኛ የግብይት ደረሰኝና የሂሳብ መዝገቦች ማቅረብ አለባቸው ” ሲል አስገንዝቧል።

አዲስ ተሽከርካሪዎች ገበያ ላይ የሚሸጡበት ዋጋ እና የሚቆርጡት ደረሰኝ ሰፊ ልዩነት እንዳለው ጥናት በማድረግ አረጋግጠናል ያለው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ገዢዎች ይዘውት የሚመጡት ደረሰኝ መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛ የተገዛበትን ዋጋ መሆን እንዳለበት እና ሲገዙም በትክክል ያወጡበትን ዋጋ መቀበል አለባቸው ብሏል።

የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ ፤ በየአመቱ ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ መኪኖች እንደሚመዘገቡ ጠቁሞ ከዚህም መንግስት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እያገኘ እንዳልሆነ ጥናቶች በተጨባጭ አረጋግጠዋል ሲል አሳውቋል።

በተቋሙ ማንኛውንም አገልግሎት የሚፈልግ ሰው ለገዛው የመኪና ዋጋ ትክክለኛ ደረሰኝ ይዞ መገኘት አለበት ስሊ ያሳሰበው ባለስልጣን መ/ቤቱ ይህ ካልሆነ ግን በተጠናውና ወደ አሰራር በተገባው መሠረት የሚጠበቅበትን ከፍሎ አገልግሎት ያገኛል ባቧል።

በዘርፉ የመንግስትን ጥቅም ለማስከበር ሁለቱም ተቋማቶች በጋራ እየሰሩ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን ፦ ገዢም ሆነ ሻጭ ትክክለኛ የሂሳብ መዝገብ ፣ ትክክለኛ ደረሰኝ መቁረጥ እና ወደ ህጋዊ አሰራር መግባት  እንደሚኖርባቸውና ትክክለኛ ዋጋ ባለማቅረብ እና ዝቅ አርጎ ዋጋን ማቅረብ ስለሚያስጠይቅ ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡ በአፅንኦት አሳስበዋል።

መረጃው የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ነው።