
ጋምቤላ 10 ሰዎች ሲገደሉ 12 ሰዎች ከባድ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ቅዳሜ ዕለት ከደቡብ ሱዳን በመነሳት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ወደ ጋምቤላ ክልል ኑዌር ዞን የገቡ የ ” ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ” 10 ሰዎችን ገድለው 12 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ማድረሳቸውን ከጋምቤላ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ታጣቂዎቹ ቅዳሜ ምሽት 3 ሰዓት ተኩል ገደማ ድንበር ጥሰው በመግባት በማኩዌይ ወረዳ ቢልኬች ቀበሌ እንዲሁም በዋንቱዋ ወረዳ መተሀር ከተማ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በፈፀሙት ጥቃት በአጠቃላይ 10 ሰዎችን ገድለው ፤ 12 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት አድርሰዋል።
በጥቃቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ወደ ጋምቤላ ጠቅላላ ሆስፒታል ለህክምና የተላኩ ሲሆን ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ደግሞ በኝንኛንግ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።
ከጥቃቱ በኃላ በጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኑዌር ዞን በሙርሌ ጥቃት የደረሰባቸውን ዜጎች ምልከታ አድርጓል።
አቶ ቴንኩዌይ ጆክ ፤ በተደጋጋሚ ወቅትና ጊዜ እየጠበቁ ጥቃት የሚሰነዝሩት የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች፣ ትቅዳሜ ምሽት ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት ነው ጥቃቱን ያደረሱት ብለዋል።
የክልሉ መንግስት ጥቃት አድራሾችን ተከታትሎ ለማደን ጥረት እያደረገ ነው ያሉ ሲሆን ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈፀም የተጠናከረ ጥበቃ ይደረጋል ብለዋል።
የክልሉ መንግስት በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደምም እነዚሁ ድንበር ጥሰው የሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በኑዌር ዞንና አኙዋ ዞኖች ገብተው የተለያዩ ጥቃቶችን ማድረሳቸው ይታወሳል።
ድንበሩ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ህብረተሰቡ በንቃት አካባቢውን እንዲጠብቅ ጥሪ ቀርቧል።
መረጃው ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬተሪያት የተገኘ ነው።