
ከ 4 ሰአት በፊት
ቻይና በማይክሮን ኩባንያ የሚመረተውን ለኮምፒውተር እና ስልክን ጨምሮ ለበርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች እንደ መረጃ ቋት እንዲሁም ኤሌክትሮኒክ አስተላላፊ ሆኖ የሚያገለግለውን ‘ሜሞሪ ቺፕስ’ ከአገሯ ገበያ አገደች።
ቻይና ይህን ያደረገችው ለብሔራዊ ደኅንነቴ አደጋ ስለሆነ ነው ብላለች።
አሜሪካ የቻይናን ድርጊት በማውገዝ ውሳኔው የኢኮኖሚ አሻጥር ነው ስትል አጣጥለዋለች።
የቻይና የሳይበር ደኅንነት መሥሪያ ቤት ትናንት እሑድ ባስተላለፈው ውሳኔ ነው፣ ይህ በአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያ በሆነው ማይክሮን የሚመረተው ‘የመረጃ መቋጠሪያ እና ኤሌክትሮኒክስ ማስተላለፊያ’ ግብአት በቻይና ገበያ ዝር እንዳይል ያለችው።
የዓለም የምጣኔ ሃብት ቀዳሚ እና ተከታይ የሆኑት አሜሪካ እና ቻይና በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ።
በተለይም በዚህ የአውራ ጣት ጫፍ በምታክለውና ለኤሌክትሮኒክስ ምርት ወሳኝ ግብአት በሆነችው ማይክሮ ቺፕስ ዙርያ ሁለቱ አገራት ብዙ እሰጣገባ ውስጥ ቆይተዋል።
ሁለቱም አገራት አንዱ የሌላውን ኩባንያ በደኅንነት ሥጋት ይከሳል።
አሜሪካ ‘ቲክቶክ’ የዜጎችን መረጃ ይቃርማል የሚል አቤቱታ በተደጋጋሚ አሰምታለች።
ይህ በአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ማይክሮን የሚመረተውን ‘ቺፕስ’ ቻይና ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ማገዷ ዋሺንግተንን አስቆጥቷል።
- የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ከሰኞ ጀምሮ ለሰባት ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ21 ግንቦት 2023
- “ተለያይቶ ትዳርን” ምንድን ነው? ጥንዶች ስለምን ይህንን ይመርጣሉ?ከ 5 ሰአት በፊት
- ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የልዑል አለማየሁን አጽም ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረከ 5 ሰአት በፊት
የቻይና የሳይበር ደኅንነት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት እንዳለው እነዚህ በመጠናቸው ደቃቅ የሆኑ የመረጃ መቋጠሪያ ቋቶች ለቻይና የኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ግንባታ “ከደኅንነት አንጻር አደጋ ናቸው።”
መሥሪያ ቤቱ በደፈናው “አደጋ ናቸው” ከማለት ውጪ እንዴት አደጋ ሊሆኑ እንደቻሉ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
የማይክሮን ኩባንያ ሕዝብ ግንኙነት ለቢቢሲ እንዳረጋገጠው ድርጅቱ ከቻይና የሳይበር ደኅንነት ቁጥጥር ባለሥልጣን እግድ ደርሶታል።
“ሁኔታውን እየገመገምን ነው። ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው። በቀጣይ የምንወስደውን እርምጃ የምናሳውቅ ይሆናል” ብሏል ማይክሮን ኩባንያ።
ባለሙያዎች ይህ እርምጃ ቻይና አሜሪካንን ለመበቀል የወሰደችው ነው ይላሉ።
እርምጃው ፖለቲካዊ እንደሆነም ይጠረጥራሉ።
አሜሪካ ባለፉት ዓመታት ግዙፍ የ ‘ኮምፒውተር ቺፕስ’ አምራች የሆነችው ቻይና መረጃ ለመቃረም ትተጋለች ስትል ክሶችን ታቀርባለች።
የትራምፕ አስተዳደር ለዋጋ ተወዳዳሪነት ሲባል በቻይና የሚመረቱ እና የኮምፒውተር እንዲሁም የስልክ መረጃ ማከማቻ እና ማስተላለፊያ ‘ቺፖችን’ በአሜሪካ ምድር ለመሥራት ብዙ ርቀት መሄዱ ይታወሳል።
ቻይና ይህን እርምጃ የወሰደችው በምህጻሩ ቡድን-7 የሚባሉት የብልጹግ አገራት መሪዎች በጃፓን ሄሮሺማ ጉባኤያቸውን ባጠናቀቁበት ዕለት ነው።
መሪዎቹ ቻይና እና ኢኮኖሚዋ ለዓለም ስጋት እንደሆኑ የሚያወሳ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።
ጆ ባይደን በሄሮሺማው ጉባኤ “የቻይናን ስጋት መመከት እና ከቻይና ያለንን ግንኙነት መልከ ብዙ ማድረግ አንዱ መፍትሄ ነው” ብለው ነበር።
ይህን ማለት የምርት ሰንሰለቶች ውስጥ ሁልጊዜም ትልቅ ቦታ በምትይዘው ቻይና ላይ ብቻ ጥገኛ ከመሆን የምርት ሰንሰለቱን ማብዛት አንዱ አማራጭ ነው ብለዋል።
የማይክሮን ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንጃይ ሜሮትራ የሂሮሺማውን የብልጹግ አገራት ጉባኤን ከታደሙ ቁልፍ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት ይህ ኩባንያ በጃፓን ምርቱን ለማስፋፋት የ3.6 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ዕቅዱን ይፋ አድርጎ ነበር።