ፌስቡክ

22 ግንቦት 2023, 13:35 EAT

የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ የተጠቃሚዎቹን ግላዊ መረጃ በአውሮፓ እና በአሜሪካ መካከል ሲያስተላልፍ በአግባቡ አልያዘም በሚል 1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ (1.2 ቢሊዮን ዩሮ) ቅጣት ተጣለበት።

ይህ በሜታ ላይ በአየርላንድ የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽን የተጣለው የገንዘብ ቅጣት፣ በአውሮፓ አጠቃላይ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ደንብ ሕግ መሠረት የተላለፈ ከፍተኛ ቅጣት ነው።

በሕጉ መሠረት ተቋማት የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ ለመጠቀም ሲፈልጉ ፈቃዳቸውን መጠየቅ እና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

ሜታ “ምክንያታዊ ያልሆነ እና አላስፈላጊ” ያለውን የተላለፈበትን ቅጣት በተመለከተ ይገባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል።

ለቅጣቱ ምክንያት የሆነው የተጠቃሚዎችን መረጃዎችን ከአውሮፓ ኅብረት ወደ አሜሪካ ያስተላለፈበት የተለመደ የኮንትራት አንቀጽ እንደሆነ ተመልክቷል።

በአውሮፓ ኮሚሽን የተዘጋጀው ሕጋዊ ኮንትራት፣ ማንኛውም ግላዊ መረጃ ከአውሮፓ ውጪ በሚሸጋገርበት ጊዜ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑ መረጋገጥ እንዳለበት የሚገልጽ ነው።

ነገር ግን በሽግግሩ ወቅት የአውሮፓውያን መረጃዎች በአሜሪካ ባለው ደካማ የግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕግ ምክንያት ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት እጅ ውስጥም ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

አብዛኞቹ ድርጅቶች ያለውን መደበኛ ደንብ መሠረት በማድረግ የኢሜይል አድራሻዎችን፣ የስልክ ቁጥሮችን እና የገንዘብ መረጃዎችን ለባሕር ማዶ ተቀባዮች የሚያስተላልፉባቸው ውስብስብ የመረጃ መሻጋገሪያ መረቦች አሏቸው።

እናም ይህ ሰፊ የሆነ የመረጃ ማሸጋገሪያ መንገድን አጠቃቀም ባለበት ሁኔታ የተጣለበት ቅጣት ተገቢ አይደለም ሲል ተቃውሟል።

የፌስቡክ ፕሬዝዳንት ኒክ ግሌግ “በአውሮፓ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች የሚጠቀሙበትን ተመሳሳይ ሕጋዊ ዘዴን ተጠቅመን ሳለ እኛን ለይቶ በተላላፈው የቅጣት ውሳኔ አዝነናል።

“ይህ ውሳኔ ችግር ያለበት፣ ምክንያታዊ ያልሆነ እና ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ መረጃን በሚያስተላልፉ በርካታ ድርጅቶች ላይ አደገኛ የሆነ ምሳሌ የሚያስከትል ነው” ብለዋል።