
22 ግንቦት 2023, 16:48 EAT
የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተጣለበት ጊዜያዊ እገዳ ተገቢ ያልሆነ እና ሕግን ያልተከተለ ነው ሲል ተቃወመ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች መምሪያ ስር የሚገኘው መንፈሳዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተጣለበትን ጊዜያዊ እገዳ የሚገልጽ ደብዳቤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 14/2015 ዓ.ም. እንደደረሰው ገልጿል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን አግልግሎት ፈቃድ በጊዜያዊነት ያገደው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያካሄደውን ስብሰባ “የሚያውክ እና ሕዝብን ለግጭት የሚያነሳሳ መልዕክት ማሰራጨቱ ተረጋግጧል” በሚል ነው።
ይህም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር አንቀፅ 70 ከተጠቀሱት ውስጥ “የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን በሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ማነሳሳት ወይም በሃይማኖት ተከታዮች መካከል አለመቻቻል እንዲፈጠር መቀስቀስ የሌለባቸው በመሆኑ” እርምጃውን እንደወሰደ ባለሥልጣኑ እሁድ ግንቦት 13/2015 ዓ.ም. ባሰራጨው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።
ለዚህም የቴሌቪዥን ጣቢያው እሁድ ግንቦት 13/2015 ዓ.ም. ሰበር ዜና በሚል ያሰራጨው መግለጫ ከሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሚና ውጪ በመሆኑ “ከጉዳዩን አጣዳፊነት እና ሊያስከትለው ከሚችለው ጉዳት አንፃር የባለሥልጣኑ ቦርድ ዘላቂ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ” የጣቢያው ፈቃድ በጊዜያዊነት የታገደ መሆኑ አሳውቋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥንም ለቀረበበት ክስ እና ለተወሰደበት የጊዜያዊ ዕግድ ውሳኔ በደብዳቤ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ፣ የቀረበው መረጃ ከጣቢያው አላማ ጋር የሚቃረን አለመሆኑን እና የተወሰደበት እርምጃም ሕግን የተከተለ አይደለም በማለት ተቃውሞታል።
- ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት የልዑል አለማየሁን አጽም ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ22 ግንቦት 2023
- በአሜሪካ እየተስፋፋ የመጣው በይፋ ሰይጣንን ‘የማምለክ’ እንቅስቃሴ21 ግንቦት 2023
- ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን ግላዊ መረጃ በአግባቡ አልያዘም በሚል ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተቀጣ22 ግንቦት 2023
ጣቢያው ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የተያያዙ “ወቅታዊ እና ከሕጋዊ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን የማቅረብ ዓላማ” እንዳለው ገልጾ፣ ለእግዱ ምክንያት የሆነው መግለጫም በበቤተ ክርስቲያኗ እውና ባላቸው ከ10 በላይ ማኅበራት የወጣ መሆኑን አመልክቷል።
የቀረበበት “በሃይማኖት ተከታዮች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ማነሳሳት” የሚለው ክስን በተመለከተም በሰጠው ምላሽ፣ “የቤተ ክርስቲያኗ ሕግ እና ሥርዓት ይከበር፣ በአባቶች መካከል የሚስተዋለው መከፋፍል ይቅር” የሚል እንጂ በቤተክርስቲያኗም ሆነ በምእመኑ መካከል ግጭትን የሚፈጥር ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
ጨምሮም በቀረበው ይዘት ላይ “ቅሬታ ያቀረበ ወገን በሌለበት እንዲሁም ጣቢያው ሳይጠየቅ እና አቋሙን ሳያስረዳ” የተወሰደው የእግድ እርምጃ “የባለሥልጣኑን ገለልተኝነት እና ነጻነትን የሚጋፋ ሆኖ” እንደሚመለከተው የቴሌቪዥን ጣቢያው ጠቅሷል።
የቀረበው ዘገባ ስህተት ሆኖ እንኳን ቢገኝ የመገናና ብዙኃን አዋጁ የሚያዘውን ሂደት በመጣስ “ያለማስጠንቀቂያ እና ውይይት” የተወሰደው እርምጃ ተገቢውን ሂደት ያልተከተለ ነው በማለት ተቃውሞታል።
ስለዚህም የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በማኅበሩ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የጣለውን ጊዜያዊ እግድ እንዲነሳለት በደብዳቤው ጠይቋል።
ባለፈው የካቲት ወር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ችግር ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ ከባድ ውጥረት እና ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ችግር ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል።
ለዚህ ችግር ምክንያት የነበረው ከቤተክርስቲያኗ ሥርዓት እናደንብ ውጪ ሦስት ጳጳሳት ለ25 ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት መስጠታቸው ሲሆን፣ ይህ ችግር ኋላ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሸማጋይነት ተፈትቶ ቆይቷል።
ያንንም ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሳምንት በፊት ጀምሮ በስብሰባ ላይ ሲሆን፣ ከሚሰሙ ጭምጭምታዎች ውጪ አስካሁን በይፋ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጠ መግለጫ የለም።
ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጊዜያዊ እግድ ምክንያት የሆነው መግለጫም የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ እያካሄደ ካለው ያልተቋጨ ስብሰባ ጋር የተያያዘ ነው።