ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ
የምስሉ መግለጫ,ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ የሲኖዶሱ ጉባኤ ከመጀመሩ በፊት መግለጫ ሲሰጡ

ከ 8 ሰአት በፊት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሳምንት በላይ በተራዘመው ስብሰባው ብዙ ባነጋገረው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ሰኞ አመሻሽ ላይ አሳወቀ።

ባለፉት ወራት በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከተከሰተው ችግር ውስጥ ዋነኛ ጉዳይ የነበረው ሹመት ጉዳይ የሲኖዶሱ ጉባኤ የመጨረሻ አጀንዳ ሆኖ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ መወሰኑ ተገልጿል።

የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ.ም. ባካሄደው ውይይት ነው በአወዛጋቢው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ በስምምነት ውሳኔ ላይ የደረሰው።

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ እና በሰሜን አሜሪካ የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ በሰጡት መግለጫ በቤተክርስቲያን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የተሳካ ውይይት ተካሂዶ “ቤተ ክርስቲያኗን የሚጠቅም ውሳኔ ተላልፏል” ብለዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ውሳኔው ችግር ላለባቸው እና አስፈላጊ በሆኑባቸው አህጉረ ስብከቶች ዘጠኝ አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት በዕጩነት የለየ ሲሆን፣ በመጪው ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም. ይሾማሉ ተብሏል።

ከእነዚህ ከታጩት ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሰባቱ በኦሮሚያ እንዲሁም ሁለቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ለሚገኙ አህጉረ ስብከቶች የሚመደቡ መሆናቸው ተገልጿል።

ነገር ግን በቀጣይ ይሾማሉ ተብለው ስለተለዩት ስለዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት ማንነት የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

በቀጣይም ለሚከናወን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት አስመራጭ ኮሚቴ ሲኖዶሱ የሰየመ ሲሆን፤ እነሱም ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ (ከሰሜን ወሎ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ)፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ (ከሐዲያ ከምባታ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) እና ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ከደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ናቸው።

ኮሚቴው እስከ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም. ዕጩዎቹን ለይቶ እንደሚያቀርብ እና ዕጩዎቹ በቅዱስ ሲኖዶሱ ተገምግመው ሹመታቸው ሲጸድቅ ሐምሌ 9/2015 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩ ሹመታቸው ይፈጸማል ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት በሚኖረው የሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ ደግሞ፣ ለአማራ፣ ለሶማሌ፣ ለድሬዳዋ፣ ለቄለም ወለጋ እና ለአሶሳ አህጉረ ስብከቶች የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሰጥ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ባለፈው አርብ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠየቅም አስከዚህ ሳምንት መቀጠሉ ይታወቃል።

ለጉባኤው መራዘም ዋነኛው ምክንያት በአከራካሪው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ ከመግባባት ላይ ሳይደረስ በመቅረቱ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና ምሥራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይኸው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጉዳይ ብዙ እንዳወያየ እና ረጅም ጊዜ መውሰዱን አረጋግጠዋል።

ለኦሮሚያ 15 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ቀርበው እንደነበረ እና በዚህም መስማማት ሳይቻል ጊዜ የፈጀ ውይይት መደረጉንና ይኸው ጉዳይ ያለመግባባት ምንጭ ነበር ብለዋል።

በመጨረሻም በዘጠኙ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ላይ በመግባባት ከስምምነት ላይ እንደተደረሰ እና በቀጣይ የሚቀርቡ ዕጩዎችን ለመለየትም ኮሚቴ መመሥረቱን አቡነ ሳዊሮስ ገልጸዋል።

ባለፈው የካቲት ወር አቡነ ሳዊሮስን ጨምሮ ሦስት ጳጳሳት ከቤተ ክርስቲያኗ እውቅና ውጪ 25 ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾማቸው ውዝግብ እና ከባድ ቀውስ ተከስቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በተለያዩ አካባቢዎች በፈጠሩ ችግሮች የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

ሹመቱን የሰጡት እና የተቀበሉት አባቶች በሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ ተወግዘው ከቤተክርስቲያኗ እንዲለዩ የሚያደርግ ውሳኔ ተለልፎባቸው ነበር።

በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተካረረ ሄዶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ሽምግልና መግባባት ተፈጥሮ ችግሩ እንዲፈታ መደረጉ ይታወሳል።