May 23, 2023 – BBC Amharic 

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ

ከ 5 ሰአት በፊት

ግብፅ የአረብ አገራት ሊግን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የምታደርገው ጥረት በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የተገባውን የመርሆዎች ስምምነትን የጣሰ ነው ስትል ኢትዮጵያ ወቀሰች።

የግብፅንም አካሄድ “ቀናነት የጎደለው’ ሲልም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ግንቦት 14/ 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ተችቷል።

የአረብ ሊግ አገራት ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም እና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ እየወሰደች ካለችው “የተናጥል እርምጃ እንድትቆጠብ” ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው ኢትዮጵያ ይህንን ምላሽ የሰጠችው።

የአረብ አገራት የመሪዎች ጉባኤ ግንቦት 11 ያስተለላፈውንም ውሳኔ ግብፅ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የምታደርገውን “ፀብ አጫሪ ትርክትን ያስተጋባ” መሆኑ ኢትዮጵያን ያሳዘነ እንደሆነ ነው መግለጫው የጠቀሰው።

መግለጫው ሊጉ ያስተላለፈው ውሳኔ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጉዳይ በሰላማዊ ድርድር መፍትሄ ለመስጠት እየጣሩ ያሉትን “የአፍሪካ ኅብረት እና አባል አገራቱን የናቀ ነው” ብሏል።

እንዲሁም “የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ሕዝቦች የሚጋሩትን የጋራ ታሪክ እና ወዳጅነት የሚጻረር ነው” ሲልም መግለጫውን ተችቷል።

የአረብ አገራት ሊግ መሪዎች ጄዳ ሳዑዲ አረቢያ ላይ አድርገውት በነበረው ጉባኤ ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ውሳኔን ማስተላለፋቸው ተዘግቧል።

ሊጉ “የግብፅ እና የሱዳን የውሃ ደኅንነት የአረብ ውሃ ደኅንነት አካል” መሆኑን በመግለጽ አገራቱ በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን መብት የሚነካ ማንኛውንም እርምጃ ውድቅ አድርጓል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በተናጥል የማድረጉ ሁኔታ መቀጠሉ “ስጋት” እንዳጫረበት የገለጸው የሊጉ ውሳኔ፣ “የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንቦችን የሚጻረር እንዲሁም የግብፅን እና የሱዳንን የውሃ ጥቅም የሚጎዳ ነው” ብሎታል።

“የሕዳሴው ግድብን ሙሌትንም ሆነ ሥራን ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ላይ ሳይደረስ በተናጠል ከሚደረግ እርምጃም መቆጠብ” እንደሚገባም አሳስቧል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ እያከናወነችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታም ሆነ ሙሌት በአውሮፓውያኑ 2015 ሦስቱ አገራት በደረሱበት የትብብር መግለጫ ስምምነት (የመርሆዎች ስምምነትን) በተከተለ መልኩ እንደሆነ ገልጻለች።

ስምነቱ የግድቡ ግንባታ ከሙሌቱ እና ከአሰራሩ ጋር በተያያዘ ካሉ መመሪያዎች እና ደንቦች ላይ ከሚደረገው ድርድር ጋር በትይዩ ሁኔታ እንደሚቀጥል በማያሻማ ሁኔታ መደንገጉን የኢትዮጵያ መግለጫ አስታውሷል።

የሕዳሴው ግድብ ሙሌት መጠን እና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን በተመለከተ የሦስቱ አገራት ባለሙያዎች ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ጠቅሷል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ሂደት በተጨማሪ “ግብፅ እና ሱዳን ያላቸውን ስጋት በማስተናገድም ከመንገዷ ወጥታ እየሰራች መሆኑም” ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ “የአባይን ውሃ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ ሁኔታ ለመጠቀም የተደረሰውን የመርሆች ስምምነት በማክበር እየሰራች እንደምትቀጥል” መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ “ኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃ እየወሰደች ነው” የሚለው ክስ “ሆን ተብሎ የተዛባ” እንደሆነ ነው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አመለክቷል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር በቅርበት እንደምትሰራም ተገልጿል።

“ግብፅ ጉዳዩን በበለጠ ለማባባስ የምታደርገውን” ጥረት በመቃወም ያስጠነቀቁትን የአረብ ሊግ አባል አገራትንም ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሊጉ አባላት በተለይም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት “ከውሳኔው ራሳቸውን እንደሚያገሉ እርግጠኛ መሆኑንም” ጠቅሷል።

“ግብፅ ሊጉን ያላግባብ በመጠቀም የምትቀጥል ከሆነ በታሪካዊው የአፍሪካ እና የአረብ ወዳጅነት እንዲሁም ግንኙነት ላይ መቃቃርን ሊፈጥር ስለሚችል ይህንንም ሊከላከሉ እንደሚገባ” ለእነዚህ አገራት ኢትዮጵያ መልዕክት አስተላልፋለች።

“ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን በብቸኝነት በበላይነት የመቆጣጠር ያልተገባ ጥያቄ እንድትተው” እንዲሁም የቅኝ ግዛትን ስምምነት እና በቅኝ ግዛት የተቃኘ እሳቤን በመተው በቀና ልቦና በመደራደር ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን ውጤት እንዲመጣ እንድትሰራ ኢትዮጵያ ጥሪ አድርጋለች።

የአረብ ሊግ በበኩሉ ባስተላለፈው ውሳኔ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነቱን ይወጣ ሲልም ጠይቋል።

ጉዳዩ በአረብ ሊግ ምክር ቤት የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ ላይም ሰላማዊ እልባት አስኪያገኝ ድረስ በቋሚ አንቀጽ እዲካተትም መወሰኑ ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ ግንባታውን ማከናወን ከጀመረች ከአስር ዓመታት በላይ የሆነው ግዙፉ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው።

ግብፅ ከ85 በመቶ በላይ ውሃው ከኢትዮጵያ ከሚመነጨው የአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን ይቀንስብኛል በሚል ያላትን ስጋት አጥብቃ ስታሰማ ቆይታለች።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የአረብ ሊግ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለኃያላኑ ምዕራባውያን በተደጋጋሚ ከግድቡ ጋር በተያያዘ እንዲደግፏት እየጠየቀች ትገኛለች።

ባለፉት ዓመታትም የኢትዮጵያ ከባዱ የክረምት ወቅት ሲጀምር ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን በማንሳት ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ የምትላቸውን አገራት እና ተቋማት፣ በውሃ አጠቃቀሙ ዙሪያ ሕጋዊ እና አሳሪ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር እንዲደረስ እንዲያሸማግሏት ግፊት እና ጥሪ ስታደርግ ቆይታለች።