May 23, 2023 – BBC Amharic 

የጤና ሰራተኞች

ከ 4 ሰአት በፊት

በኮሌራ መስፋፋት እጅግ የተቆጡ ደቡብ አፍሪካውያን ሰኞ ዕለት ከንቲባቸውን መንገድ ለመንገድ ሲያሳድዷቸው ታይተዋል።

ነዋሪዎቹ፤ ከንቲባው ንፁህ ውሃ ማቅረብ ተስኗቸዋል ሲል ወቀሳቸውን ያሰማሉ።

ከደቡብ አፍሪካ ግዛቶች በርካታ ሕዝብ ይኖርባታል በምትባለው ጋውቴንግ በኮሌራ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 15 ደርሷል።

የሺዋኔ ከተማ ከንቲባ ሲሊዬርስ ብሪንክ ከብሔራዊው መንግሥት ከሚመጡ ባለሥልጣናት ጋር ለመምከር ዝግጅት ላይ ነበሩ።

ከንቲባው በአካባቢው ለተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ መፍትሔ ለማበጀት ነው ከባለሥልጣናቱ ጋር ለማውራት ያቀዱት።

ነገር ግን ጁቢሊ ዲስትሪክት ሆስፒታል አካባቢ ‘ከንቲባችን ንፁህ መጠጥ ውሃ ሊያቀርቡልን’ አልቻሉም ያሉ ነዋሪዎች ግርግር ይፈጥራሉ።

በከንቲባው ሥራ የተቆጡ የአካባቢው ሰዎች በሆስፒታሉ አካባቢ ያሉ መኪናዎችን ማጥቃት ሲጀምሩ ከንቲባው ‘እግሬ አውጭኝ’ ብለው አካባቢውን ለቀው ይጠፋሉ።

ነዋሪዎቹ የጤናችንን ሁኔታ ከንቲባው ከቁብ አልቆጠሩትም ሲሉ ይወቅሳሉ።

የጋውቴንግ ግዛት ጤና ቢሮ ባለፈው እሑድ ከፕሪቶሪያ ሰሜን በምትገኘው ሃማንስክራል የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን ይፋ አደርጓል።

ከ100 በላይ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ያቀኑ ሲሆን፤ 37 ሕመምተኞች ተለይተው እንዲታከሙ መደረጉን የከተማዋ አስተዳደር ገልጧል።

አስተዳደሩ በሃማንስክራልና አካባቢዋ ያሉ ነዋሪዎች ያልተጣራ ውሃ እንዳይጠጡ አስጠንቅቋል።