![ወ/ሮ አፀደ መብራህቶም ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው ሽረ የሚገኙ [ፎቶ ከፋይል]](https://i0.wp.com/ichef.bbci.co.uk/news/640/cpsprodpb/5261/live/b96187e0-f975-11ed-92cc-b3a9bf1f67e9.jpg?w=800&ssl=1)
23 ግንቦት 2023
በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱ ከሆነው ምዕራም ትግራይ የተፈናቀሉ ሰዎች ያለሰብአዊ እርዳታ በችግር ላይ መሆናቸውን እና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚጠይቅ ሰልፍ አደረጉ።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነትን ተከትሎ ከቀያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮች በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ቢነጋ ጉዕሽ ከሚወዷቸው ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ጋር ስቀው፣ በልተው እና ጠጥተው ከሚያድሩበት የሞቀ ቤታቸውና ተከብረው ከኖሩበት ቀያቸው ከራቁ ሁለት ዓመት አልፏል።
በጦርነቱ ምክንያት ሃብታቸውን እና ንብረታቸውን አጥተው ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉት አቶ ቢነጋ፣ በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ምዕራብ ሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ያልለመዱትን የስደት ሕይወት እየመሩ ይገኛሉ።
ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይ ላይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የነበረው የሰዎች መፈናቀል “በጣም አሳዛኝ የስደት ማዕበል ይመስል ነበር” በማለት ያስታውሳሉ።
“በእግር እና በመኪና ተመምን። ያሳዝናል. . . በአንዲት ቀን ብቻ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ አካባቢውን ለቆ ወጣ” ሲሉ በተሰበረ ልብ ይናገራሉ።
አቶ ቢነጋ ጦርነቱ ለዓመታት ይዘልቃል፣ ተፈናቃዮች ሆነን ይህን ያክል ጊዜ እንቆያለን ብለው አስበው እንደማያውቁ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።
“ነገር ግን እሳቱ ተከትሎን መጣ። እስካሁን ድረስም ሽረ እንዳሥላሴ ውስጥ ቆየን።”
አሁን ግን ወደ ትውልድ መንደራቸው መመለስን እንጂ እዚያው መከራን የሚያስታውሳቸው ሁኔታ ውስጥ መቆየትን አይፈልጉም።
“ምን አድርገን ነው ወደ ቀያችን የማይመልሱን?” ብለው ይጠይቃሉ።
ይህ በትግራይ ውስጥ በተለያዩ ጊዚያዊ የተፈናቃዮች ማዕከላት የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚያነሱት ጥያቄ ነው።
ይህንን አስመልክቶ በመቀለ፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ አብዪ ዓዲ፣ ሽረና ሌሎች ከተሞች ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
አቶ ቢነጋ ሰልፉ ላይ ተሳትፈው ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመለሱ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች እንደተዘነጉ በማንሳት “እየተራብ ነን፤ ለብርድም ተጋልጠናል” በማለት በመሠረታዊ አቅርቦቶች ችግር እየተሰቃዩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
እሳቸው እንደሚሉት በሽረ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተፈናቃዮች ላለፉት ስምንት ወራት ሰብዓዊ ድጋፍ አላገኙም።
ሽረ ውስጥ ከ18 በላይ የተፈናቃዮች ማዕከላት እንዳሉ የተቋማቱ አስተባባሪዎች ይናገራሉ።
ለሦስት ዓመታት ያህል በፀሐየ ትምህርት ቤት የተፈናቃዮች ማዕከል ውስጥ ተመዝግበው እየኖሩ ያሉት አቶ ቢነጋ፣ “የፌዴራል መንግሥት ዜጎች እንደሆንን የሚያስብ ከሆነ ወደ ቀዬያችን ይመልሰን፤ ቤት አለን ወደ ቤታችን እንግባ” ሲሉ ይጠይቃሉ።
ከመፈናቀላቸው በፊት ስለነበረው ሕይወታቸው የተጠየቁት አቶ ቢነጋ በከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ሆነው “ሰቲት ሑመራ ውስጥ ሦስት ነዳጅ ማደያዎች ነበሩኝ፤ አሁን…ሰው…ሕህዝባችን የሚበላው አጥቶ ቅጠል…እየበላ ነው። በቃ ይሄ ነው፤ በሁሉም መንገድ ወድመናል” በማለት በተሰበረ ስሜት ከዚያ በላይ መናገር አልቻሉም።
- ትግራይ ውስጥ በረሃብ ምክንያት 25 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ17 ግንቦት 2023
- ትምህርት በተጀመረባት ትግራይ ጠፍጣፋ ድንጋይ በመጠቀም እያስተማሩ ያሉት መምህር12 ግንቦት 2023
- በስርቆት ምክንያት የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት በትግራይ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ አቋረጠ4 ግንቦት 2023

ዛይድ ከቃፍታ ሑመራ ባዕኸር ቀበሌ ተፈናቅላ መቀለ ውስጥ 70 ካሬ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የምትኖር የአራት ልጆች እናት ናት።
እሷ መጀመሪያ ወደ ሽረ፣ ከሽረ ደግሞ ወደ መቀለ ስትፈናቀል የፆታዊ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ሴቶች መካከል አንዷ ናት።
“እኔ የግል ምግብ ቤት እና ሆቴል የነበረኝ ራሴን ችዬ የምኖር ሰው ነበርኩ፤ አሁን ምንም ሳይኖረኝ የሌለኝ ተጎሳቁዬ እየኖርኩ ነው። ይህ ሳይበቃ ሙሉ ህክምና አናገኝም። በዚያ ላይ ረሃብ አለ፤ ሰብአዊ እርዳታ አናገኝም፤ ልጆች መማር አይችሉም። ሰው በረሃብ እየተሰቃየ ነው። በስማችን እየተነገደ ነው” ስትል ቅሬታዋን ትናገራለች።
ከ2012 ጀምሮ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በኋላም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ባፈናቀለው ጦርነት ምክንያት ሁሉም ልጆቿ ከትምህርት ገበታ በመራቃቸው እጅግ ታዝናለች።
“11ኛ ክፍል መድረስ የነበረበት ልጄ የትም እየለመነ ይውላል። ሰጪ የነበርኩ ሰው ተቀባይ ሆኜም ሳጣ፣ ብዙ ጥቃት ደርሶብኝ አእምሮዬ እፎይታ አግኝቶ ሊኖር አይችልም። ከዚህ በኋላ መንግሥት ወደ ቦታችን እንዲመልሰን ነው የምፈልገው” ትላለች።
ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅሎ መቀለ ውስጥ እየኖረ የሚገኘው ሃለቃ ሃፍታይ አብርሃም ማክሰኞ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ተሳትፏል።
ከጦርነቱ በፊት በዳቦ ቤት፣ በዶሮ እርባታና በንግድ ድርጅት ተሰማርቶ የተሻለ ሕይወት ሲመራ የነበረው ሃለቃ ሃፍታይ ጦርነቱ እንተጀመረ “የኤርትራ ሠራዊት ሲተኩሰው ከነበረው ከባድ መሳርያ ለመሸሽ ወደ መቀለ ሲነሳ “ሑመራ ውስጥ ተይዘን ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር ታሰርኩ” ሲል ያስታውሳል።
እሱ እንደሚለው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተከትሎ እሱ እና ሌሎች እስረኞች ከእስር ቤት ሲፈቱ የተከዜን ወንዝ አሻግረው እንደባረሯቸው ይናገራል።
“በሑመራ እስር ቤት በአማራ ኃይሎች ታስሬ ነበር። እዚያ ያሳለፍነው ስቃይ ነው። ከእኛ ጋር ታስረው ከነበሩት መካከል ትፈለጋላችሁ ተብለው በአማራ ታጣቂ ላይሎች የተወሰዱ 59 ምሁራን እስካሁን የት እንደገቡ አይታወቅም” በማለት ያሳለፈውን ስቃይ ይገልጻል።
በአንድ ወቅት ራሱን እና ቤተሰቡን በተሻለ ኑሮ ያስተዳድር የነበረው ይህ የትግራይ ተወላጅ ከእስር ከተፈታ በኋላ አሁን ከአራት ልጆቹ እና ከባለቤቱ ጋር 70 ካሬ በሚባለው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ነው ያለው።
“ከመጣሁ ጀምሮ እርዳታ አላገኘሁም። ለእስረኞቹ ተብሎ የተሰጠን እርዳትም ይሁን ሌላ ነገር የለም። የሚያውቀን ሰው ይረዳናል። ነገር ግን ከመንግሥትም ሆነ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች የቀረበልን ምንም ነገር የለም” ይላል።
ሃለቃ ሃፍታይ ዛሬ የተካሄደው ሰልፍ “ዓለም ሁኔታችን እንዲያይ ቀያችንን የተቆጣጠሩ የአማራ ኃይሎች እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው” ሲል ያስረዳል።
ወደ ቀዬው ቢመለስም “ንብረታችን እዚያው እያለን ነው መውሰድ የተጀመረው። ስለዚህ ንብረታችንን ይጠብቀናል የሚል ተስፋ የለንም። ግን ወደ ቦታችን ይመልሱን እንጂ ሰርተን እንለውጣለን” ሲል ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግሯል።
በሽረ የተካሄደውን ሰልፍ ያስተባበረው እና ከምዕራብ ትግራይ የተፈናቀለው አቶ ጀንበር ግርማይ በበኩሉ ተፈናቃዮቹ በትምህርት ቤቶች ሜዳ ላይ እንደሚገኙና ድንኳኖቹም በፀሐይ እና በነፋስ እንደተቀዳደዱ ያስረዳል።
የሰልፉ ዓላማ በዋናነት በስርቆት እና በብክነት ክስ የተቋረጠው ሰብአዊ እርዳታ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ ነው የሚለው ጀንበር ነጋዴ እንደነበር እና የሁለት ልጆች አባት እንደሆነ ይገልጻል። እሱ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቤተሰቡ ጋር ያሳለፈው አስቸጋሪ ህይወት እንደከበደው ነው የሚናገረው።
እሱና ቤተሰቡ “የትውልድ መንደሬ” ወደሚለው አካባቢ ተመልሰው እንደ አዲስ ህይወትን ‘ሀ’ ብሎ መጀመርን ይመኛል።
“ንብረቶቼ በሙሉ ተወስዷል። ሰርተን ወደ መደበኛው ሕይወታችን መመለስ የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። በአማራ ኃይሎች እየተሰራ ያለው ነገር መቆም እና ተፈናቃዮችም ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው” ሲል አስረድቷል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በጥቅምት 2013 በትግራይ ተጀምሮ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት በተመሳሳይ ወር 2015 በትግራይ መሪዎች እና በፌደራል መንግስት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት አብቅቷል።
ስምምነቱ ከፌደራል መከላከያ ሠራዊት ውጭ በጦርነት የተሳተፉ የአማራ እና የውጭ ኃይሎች እንዲወጡ እና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ይጠይቃል።
የአማራ ክልል መንግሥት ይገባኛል ከሚላቸው የትግራይ አካባቢዎች አንዱ የሆነው ምዕራብ ትግራይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ አስተዳደር እና በሠራዊቱ ስር እንደሚገኝ ይገለጻል።
በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር የቆየው የምዕራብ ትግራይ በ2013 ዓ.ም. የጀመረውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር ገብቶ ወልቃይት ጠገዴ በሚል የክልሉ አንድ አካል ሆኖ ይገኛል።
በአማራ ክልል በኩል በአካባቢው የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ የቆዩ ሲሆን፣ በአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች ማንነታቸው እና ክልላቸው ከአማራ ክልል ጋር መሆኑን የሚገልጹ ሰልፎች ከዚህ በፊት ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
አሁን አካባቢውን የሚያስተዳድረው የአማራ ክልል መንግሥትም ይህ ጥያቄ ሕጋዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ሲጠይቅ የቆየ ሲሆን፣ የፌደራል መንግሥቱም የወሰን ይገባኛል ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኝ ሲገልጽ ቆይቷል።