አዶልፍ ሂትለር የተወለደበት የኦስትሪያው መኖሪያ ቤት

ከ 3 ሰአት በፊት

አዶልፍ ሂትለር የተወለደበት የኦስትሪያው መኖሪያ ቤት ለፖሊስ መኮንኖች የሰብዓዊ መብት ስልጠና መስጫ ስፍራነት እንዲውል ተወሰነ።

ቤቱ ምን ይሁን በሚልም ለረዥም ጊዜ የውዝግብ ምንጭ ሆኖም ቆይቷል።

በጀርመን ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው ብራውናው አም ኢን በተባለ ግዛት የሚገኘውንም የሂትለር የትውልድ ቦታ ህንጻ ከረዥም ጊዜ ውዝግብ በኋላም መንግሥት የገዛው በአውሮፓውያኑ 2016 ነበር።

ዘር ጨፍጫፊው አምባገንን በህንጻው በላይኛው ፎቅ ላይ ቤተሰቦቹ ተከራይተውት በነበረው ክፍል የተወለደው በአውሮፓውያኑ 1889 ነበር።

ቤቱን ለማደስና ለመቀየር የሚደረገው የግንባታ ስራም በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም የሂትለር ቤት ማደስና መቀየር አከራካሪ ሆኗል።

አንዳንድ ኦስትሪያውያን ቤቱ እንዲፈርስ የፈለጉ ሲሆን ቤቱ የኒዮ ናዚዎች ማዕከል እንዳይሆንም ለመግታትም አንድ የባለሙያዎች ኮሚቴ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህንን መፍረስ የተቃወሙ ተቺዎች የኦስትሪያን ያለፈ ታሪክ መፋቅና መካድ ነው ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ በበኩላቸው ቤቱ እንደ እርቅ ወይም እንደ የበጎ አድራጎት ድርጅት ቅጥር ግቢ ሊያገለግል ይገባል ይላሉ።

በአዲሱ ዕቅድ መሰረት የግንባታ ስራዎች በአውሮፓውያኑ 2025 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሚቀጥለው ዓመትም የፖሊስ ኃይል ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም የኦስትሪያ ብሮድካስት ኦአርኤፍ ዘግቧል።

በናዚ የአገዛዝ ዘመን ቤቱ ለሂትለር የመዝናኛ ስፍራ እንዲሆንም ተቀይሮ ነበር። ሆኖም ከተማዋ የቱሪስት ማዕከል መሆኗን ተከትሎ ሂትለር በዚያች ቤት ውስጥ የኖረው ለጥቂት ወራት ብቻ መሆኑም ተገልጿል።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1944 ናዚዎች ስልጣን ማጣታቸውን ተከትሎ ቤቱም አገልግሎት መስጠት አቁሞ ነበር።

በኋላም ለበርካታ አስርት ዓመታት የኦስትሪያ መንግሥት የቀኝ ጽንፈኝነት ቱሪዝምን ለመግታት በሚል ቤቱን ከቀድሞ ባለቤቱ ጀርሊንዴ ፖመር ተከራይቶት ነበር።

ባለቤቷ በቤቱ ላይ እድሳት እንዳይደረግ እስከለከለችበት ጊዜ ድረስ የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ ሰዎች እንደ የቀን እንክብካቤ ማዕከልነትም ውሏል።

በአውሮፓውያኑ 2016 መንግሥት ቤቱን ከባለቤቷ ለመውሰድ የሚፈቅድ ህግ በማውጣትም በምላሹ 800 ሺህ ዩሮ በላይ ካሳም ሰጥቷታል።

ከሶስት ዓመታት በኋላም የኦስትሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የ17ኛውን ክፍለ ዘመን ቤት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመቀየር ማቀዱን አስታወቀ።

ኦስትሪያ በአውሮፓውያኑ 1938 በናዚ ጀርመን ወረራ የተፈጸመባት ሲሆን ለበርካታ አስርት ዓመታት የናዚ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል የመጀመሪያዋ እንደሆነች ስትናገር ቆይቷል።

ነገር ግን በወቅቱ ብዙዎች አንሹሊስ ወይም ግንኙነት ለተባለው የናዚ ጀርመን እርምጃ ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን ኦስትሪያም በአሁኑ ወቅት በናዚ የጭፍጨፋ ወንጀል የነበራትንም ተሳትፎም አምናለች።