አሜሪካ ሰራሽ ሃምቪስ

ከ 4 ሰአት በፊት

አሜሪካ የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ ከተፈጸመው ጥቃት ራሷን አራቀች።

ሩሲያ በዩክሬን በኩል ድንበር አልፈው የገቡት ታጣቂ አማጺያን ሽንፈት ገጥሟቸዋል ብላለች።

ሩሲያንና ዩክሬን ከሚያዋስናቸው አንዱ በሆነው የቤልጎሮድ ግዛት በኩል ሰኞ እለት ታጣቂዎች ገብተው ጥቃት ፈጽመዋል ተብሏል።

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከፈጸመች በኋላም የሩሲያን ድንበር የተሻገረ ወረራ ሲፈጸም የመጀመሪያው ነው።

ሩሲያ በቤልጎሮድ ግዛት አሜሪካ ሰራሽ ሃምቪስን ጨምሮ በርካታ ከጥቅም ውጭ የሆኑ የምዕራባውያን ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ምስሎችን አውጥታለች።

አሜሪካ በበኩሏ “ በሩሲያ ውስጥ ጥቃቶችን አላበረታታንም” ስትል ተናግራለች።

በዚህ ጥቃት ላይ አሜሪካ ያቀረበችው የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን በተመለከተ በማህበራዊ ሚዲያና በሌሎችም መድረኮች ላይ እየተሰራጩ ያሉ ዘገባዎችን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምነዋል።

ነገር ግን አገራቸው “የእነዚህ ዘገባዎች ትክክለኛነትን በተመለከተ በዚህ ጊዜ ትጠራጠራለች” ብለዋል።

ማቲው ሚለር ማክሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህንን ጦርነት እንዴት መምራት እንዳለባት የመወሰን የዩክሬን ጉዳይ ነው” ሲሉ አክለዋል።

በድንበር አቅራቢያ የሚገኙ የቤልጎሮድ መንደሮች ነዋሪዎች በደረሰው ከባድ መሳሪያ ጥቃት ተፈናቅለዋል።

ሩሲያ 70 የሚሆኑ ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጻ እነዚህም ዜግነታቸው ዩክሬናውያን ናቸው ብላለች።

ዩክሬን ከዚህ ጥቃት ጀርባ እጄ የለበትም ያለች ሲሆን ድንበር ተሻግረው የወረሩትም የሩስያ ዜግነት ካላቸው ሁለት ወታደራዊ ቡድኖች የተውጣጡ ታጣቂዎች ናቸው ብላለች።

በተጨማሪም ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉት የሩሲያ ሌጌዎን ነጻነት እና የሩስያ በጎ ፈቃደኞች ኮርፕስ የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች ናቸው ብላለች።

የሩስያ ሌጌዎን ነጻነት መቀመጫውን በዩክሬን አድርጎ የሩስያን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ከስልጣን ለመገርሰስ እየሰራ እንደሆነ ይገልጻል።

ሰኞ ዕለት የተከሰተውን ወረራ ተከትሎ በግዛቲቷ “የፀረ-ሽብር ዘመቻ” የተጀመረ ሲሆን ይህም የአካባቢው ባለስልጣናት የማንነት ቁጥጥር፣ የህዝብ እንቅስቃሴ መግታት እና የግንኙነት ክትትል እንዲያደርጉም ልዩ ስልጣን ሰጥቷቸዋል።

ዩክሬን ከሩስያ በኩል የቀረበባትን ክስ ውድቅ ብታደርግም ይህ ወረራ ከዩክሬን ወታደራዊ መረጃ እርዳታ ውጭ ተፈጽሟል ብሎ ማመን ከባድ ነው።