
ከ 1 ሰአት በፊት
ክሬምሊን አሻጥረኞች ትላቸዋለች። ዩክሬን በጭራሽ የኔ ዜጎች አይደሉም ብላለች። አሜሪካ እኔን እዚህ ውስጥ አትክተቱኝ ስትል ራሷን ታርቃለች።
እነዚህ የሩሲያን ድንበር ደፍረው በመሻገር ክሬምሊንን የሚፋለሙ ሚሊሻዎች ማን ናቸው ግን?
ሰሞኑን ነው ጥቃት የከፈቱት። ጥቃት መከፈቱን ሩሲያም አምናለች።
ሁለቱ ሚሊሻ ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት እንደተበታተነ የሩሲያ መገነኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
“70 የሚሆኑትን ገድለናል፤ ቀሪው ጨርቄን ማቄን ሳይል ወደመጣበት ዩክሬን ተፈትልኳል” ብሏል የክሬምሊን ቃል አቀባይ።
የነዚህ ማንነታቸው በውል ያልታወቀው ሚሊሻዎች ጥቃት ሁለት ቀናት ሙሉ የወሰደ ነው።
አንድ ኃይል የሩሲያ ድንበርን ደፍሮ ገብቶ ጥቃት ሲፈጽም የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የመጀመርያው ነው።
ሩሲያ ተዋጊዎቹ ‘ምን ጥያቄ አለው፤ ዩክሬናዊያን ናቸው” ብትልም ዩክሬን ግን ይህን ለማስተባበል ጊዜ አልወሰደባትም።
እንደ ዩክሬን ገለጻ ከሆነ እነዚህ ሚሊሻዎች ከሁለት ቡድን የተዋቀሩ ናቸው።
አንዱ የሩሲያ ወደ ዘማቾች ቡድን፣ በእንግሊዝኛ ምህጻሩ (RDK-አርዲኬ) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሌላው ደግሞ ‘ራሺያ ሌጂን’ የሚባል ነው።
ሁለቱም በጥምረት የሚዋጉት የፑቲንን አስተዳደር በኃይል ለመገርሰስ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ክሬምሊንን የሚዋጋው የዓለም አቀፍ ሠራዊት ጥምር ኃይል አካል ተደርገው ሲጠቀሱ ነበር።
የኪየቭ የደኅንነት መሥሪያ ቤት መኰንን የሆነው አንድሪ ዩሶቭ ሁለቱ ቡድኖች ራሳቸውን ችለው በሩሲያ ምድር የሚንቀሳቀሱ ሚሊሻዎች ናቸው ይላል።
እርሱ፣ ‘ዩክሬን በነርሱ ጦር ጣልቃ አትገባም’ ሲል ይደመድማል።
የዩክሬን ብሔራዊ ቴሌቪዥን በበኩሉ እነዚህ ቡድኖች የሩሲያ ዜጎች ናቸው ይላል።
የሩሲያ ወዶ ዘማቾች ቡድን ወይም (RDK) በመጋቢት 2023 ድንበር ላይ በወሰደው ጥቃት ነው ለመጀመርያ ጊዜ ስሙ የገነነው።

ያልተረጋገጡና ከሩሲያ የወጡ ዘገባዎች ቡድኑ ተኩስ ከፍቶ፣ ጉዳት አድርሶ፣ ሰዎችን አፍኖ ከሩሲያ ግዛት መውጣቱን ቢገልጹም ቡድኑ ግን ሩሲያዊያን መንግሥታቸው ላይ እንዲያምጹ ከመቀስቀስ ባሻገር አፍኖ የወሰዳቸው ሰዎች እንደሌሉ ተናግሯል።
የዚህ ቡድን መሪ ዴኒስ ካፑስቲን ወይም ደግሞ በስፋት ዴኒስ ኒኪቲን ይባላል።
የሩሲያ ብሔርተኛ ሲሆን እርሱ የሚመራው ቡድን አንዲት በብሔር ያልተከፋፈለች ኅብረ ብሔራዊ የሆነች ወጥ ሩሲያን ለመፍጠር እታገላለሁ ይላል።
- አሜሪካ የሩሲያን ድንበር አልፎ ከተፈጸመው ጥቃት ራሷን አራቀችከ 4 ሰአት በፊት
- የልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ቤተሰቦች ጥያቄ እና የንጉሣውያኑ ቤተ መንግሥት ምላሽከ 5 ሰአት በፊት
- የሂትለር ቤት ለፖሊስ የሰብዓዊ መብት ስልጠና መስጫነት ሊውል ነውከ 3 ሰአት በፊት
በ202 ዓ/ም አንድ የዩክሬን ድረ-ገጽ ሰውየው ከአፍቃሪ ናዚ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳለው ደርሼበታለሁ ሲል ነበር።
ዴኒስ ኒኪቲን ከዚህ ቀደም ራሱ እንዳመነው ደግሞ በዓለም ላይ የሚገኙ የእግር ኳስ ነውጠኞች ጋር ግንኙነት እንዳለውና ድጋፍም እንደሚያደርግ ጠቅሷል።
ሰውየው የሩሲያ ተቃዋሚዎች በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ አቋም አለመውሰዳቸውን ደጋግሞ ይተቻል።
ሌላ ከዚሁ ቡድን ጋር ተቀራራቢ የሆነው ሚሊሻ ‘ፎርቱና’ ይባላል።
ባለፈው ወር ይህ ቡድን ለዩክሬን ሚዲያ እንደተናገው የቡድኑ አባላት 120 መሆናቸውን ጠቅሶ፣ “በጎ ፈቃደኛ ተዋጊዎች ስብስብ እንጂ ቅጥረⶉች አይደለንም፤ እንደ ዩክሬናዊያን ውትድርና ተመልምለንም አይደለም ፑቲንን የምንፋለመው” ብሏል።
ሌላው ዋናው የሚሊሻ ቡድን ‘ሊበርቲ ኦፍ ራሺያን ሌጂን’ ወይም በእንግሊዝኛ ሆሄያት ምሕጻር (FRL) የሚባለው ቡድን ነው።
ባንዲራቸው መደቡ ‘ነጭ-ሰማያዊ-ነጭ’ ያለበት ሲሆን የዚህ ቡድን አባላት ሩሲያን ነጻ ለማውጣት እንደሚታገሉ በሩሲያ ተቃዋሚዎች ዘንድ ይታመናል።
ዴኒስ ኒኪቲን እንደሚለው የርሱ ቡድንም ሆነ ይህ ‘ሊበርቲ ኦፍ ራሺያን ሌጂን’ ቡድን የሚዋጉት ፑቲንን ከክሬምሊን ለመንቀል ቢሆንም ይህ ቡድን ግን እርሱ ከሚመራው ቡድን ጋር ሲነጻጸር ለዘብተኛ እንደሆነ ይናገራል።
ከዚህ ቀደም በግንቦት 22 ይህ ቡድን ኮዚንካ የምትባልን የሩሲያ መንደር ‘ነጻ አውጥተናታል’ ብሎ አውጆ ነበር።
ይቺ መንደር ከዩክሬን ድንበር እልፍ ብላ የምትገኝ ናት። ከቤልጎሮድ ደቡብ ምዕራብ በኩል ናት።
ቡድኑ ይቺን መንደር ከተቆጣጠረ በኋላ “መላውን የቤልጎሮድ አካባቢ ከፑቲን ነጻ እናወጣለን’ ብሎ ሲዝት ነበር።
“ሩሲያ ሁሌም አትደፈርም፤ ሕዝቧም ስጋት አይገባውም የሚለውን አስተሳሰብ እንደሚገረሰስ ለማሳየት ነው መንደሯን የተቆጣጠርናት” ብሏል ቡድኑ።
በቡድኑ የተለቀቀ ተንቀሳቃሽ ምሥል የቡድኑን ባንዲራ ከሩሲያ ባንዲራ በላይ ከፍ አድርጎ በፊኛ ላይ አንጠልጥሎ ሲሰቅል ያሳያል።
ይህ ጦር አቅሙ ምን ያህል ነው የሚለው ግልጽ ባይሆንም በድረ-ገጹ ላይ ግን ከዩክሬን ጋር በጥምረት እንደሚሠራና በዩክሬን ሠራዊት ዕዝ ሥር እንደሚንቀሳቀስ ይጠቅሳል።
ሩሲያ ይህን ቡድን “አሸባሪ’ ብላ ለመበየን እያሰላሰለች ነው። ኾኖም ግን ከዚህ ቀደም የቡድኑን ሕልውና ስለካደች አሁን ‘አሸባሪ’ ብሎ መበየን አስቸጋሪ ሳያደርግባት የቀረ አይመስልም።
አንዳንዶች ይህ በሁለት ቡድኖች የተዋቀረ ትንሽ የሚሊሻ ኃይል በጦር ሜዳ ያለው ጠቀሜታ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ይላሉ።
ዩክራናዊው ቭላድሚር ፌሴንኮ የተባለ የወታደራዊ ተንታኝ የቡድኖቹ መኖር ፋይዳው ይበልጥ ወታደራዊ ሳይሆን የፕሮፓጋንዳ ሚና ነው ይላል።
በዚህ የማይስማሙ የጦር ተንታኞች ግን ቡድኖቹ አሜሪካ ሠራሽ ጦር መሣሪያ መታጠቃቸው ድጋፋቸውና ከጀርባ ያላቸውን ኃይል አመላካች በመሆኑ አቅማቸው በዋዛ ሊታይ አይገባም ይላሉ።
አሜሪካ ሁሌም እንደምትለው በሩሲያ ምድር የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ‘አላበረታታም’ ብላለች።
ከነዚህ ታጣቂ ሚሊሻዎች ጋር ስሟ እንዲነሳም የፈለገችም አይመስልም።
‘ይህን ጦርነት እንዴት መምራት እንዳለባት የመወሰን የዩክሬን ጉዳይ ነው’ ብላለች አሜሪካ።
የቀድሞው የሩሲያ የምክር ቤት አባልና የአሁኑ የዩክሬን ዜጋ ኢሊያ ፖናሜሬቭ በነሐሴ፣ 2022 በፌስቡክ ገጻቸው የሚከተለውን ጽፈው ነበር።
“ሁለቱ ቡድኖችና ናሽናል ሪፐብሊካን አርሚ የተሰኘው ሌላ ሦስተኛ ቡድን ሩሲያን በፑቲን መዳፍ ፈልቅቆ ለማውጣት የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸውን አውቃለሁ።”