ኮማንደር ዴኒስ ካፑስቲን
የምስሉ መግለጫ,ኮማንደር ዴኒስ ካፑስቲን

ከ 4 ሰአት በፊት

ባሳለፍነው ሰኞ የሩሲያን ድንበር ሰብረው እንደገቡ የተነገረላቸው ሽምቅ ተዋጊዎች ተመሳሳይ እርምጃ እንፈጽማለን ሲሉ ዛቱ።

ከነዚህ ሸማቂ ቡድኖች አንዱ የሆነው የሩሲያ ወዶ ዘማቾች ቡድን መሪ ዴኒስ ካፑስቲን በዩክሬን መሬት ላይ ሆኖ እንደተናገረው ‘በቅርቡ በሩሲያ በኩል ገብተን የምታዩን ይመስለኛል’ ሲል እሱ የሚመራው የአርዲኬ (RDK) ቡድን ለሌላ ዙር ጥቃት መሰናዳቱን ጠቁሟል።

ይህ ቡድን የሩሲያን ድንበር አልፎ ገብቶ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የቡድኑ ማንነት ብዙ ሲያነጋግር ነበር።

በኋላ ላይ በወጡ መረጃዎች ሁለት ቡድኖች ተዋቅረው የፈጸሙት ጥቃት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ቡድኖቹም በአማጺ ሩሲያዊያን ተዋጊዎች የተመሠረቱ ሲሆን አርዲኬ (RDK) እና ሊበርቲ ኦፍ ራሺያ ሌጂን (LSR) የሚል ስም አላቸው።

ሁለቱም ቡድኖች ሩሲያን ከፑቲን እጅ ነጻ ለማውጣት ይታገላሉ።

ሩሲያ በበኩሏ የቡድኑ አባላት ዩክሬናዊያን ናቸው ትላለች።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ይህ ቡድን ድንበር ተሻግሮ ጥቃት መፈጸሙን አምኖ ነገር ግን “የማያዳግም እርምጃ ወስጄባቸዋለሁ፤ 70 ገድያለሁ፤ ሌሎቹ እግሬ አውጪኝ ብለው ወደመጡበት ተመልሰዋል” ሲል በመግለጫው አትቷል።

ትናንት ረቡዕ የአርዲኬ (RDK) መሪ ካፑስን በዩክሬን ድንበር ሆኖ በሰጠው መግለጫ “በወሰድነው እርምጃ ረክተናል” ብሏል።

የርሱ ሸማቂ ቡድን የተወሰኑ መሣሪያዎችን ከሩሲያ ወታደሮች መውሰዱንም አብራርቷል።

መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆን እስረኞችንም ይዞ ወደ ዩክሬን መመለሱን ገልጾ ጠቅላላው ኦፕሬሽን 24 ሰዓት እንደወሰደ ተናግሯል።

ሩሲያ “አሻጥረኞች” በሚል የጠራቻቸው እነዚህ ሁለት ቡድኖችን በአሸባሪነት ለመፈረጅ ሐሳብ እንዳላት ተሰምቷል።

ካፑሲን እንዳለው ሩሲያ በነርሱ ወታደሮች አደረስኩ ያለችው መጠነ ሰፊ ጉዳት ሐሰት እንደሆነና 10 ወታደሮች ቆስለው 2 መገደላቸውን ገልጧል።

በዚህ መግለጫው ካፑሲን የሚዋጉበት መሣሪያ ምዕራባዊያን ዩክሬን ራሷን እንድትከላከልበት በተሰጣት ጦር መሣሪያ እንዳልሆነ አስተባብሏል።

ይሁንና ቡድኑ መሣሪዎቹን ከየት እንዳገኘ ያለው ነገር የለም።

ሩሲያ እነዚህን ሁለት ቡድኖች የዩክሬን ሽምቅ ተዋጊዎች አድርጋ ብትገልጻቸውም ቡድኖቹ ግን እኛ በማያሻማ ሁኔታ ሩሲያዊያን ነን፤ በመሐላችን አንድም ዩክሬናዊ የለም ይላሉ።

ዓላማቸውም ፑቲንን ከሥልጣን አንስቶ ሩሲያን ነጻ ማድረግ እንደሆነ ያብራራሉ።

ዴኒስ ካፑስቲን በትናንቱ መግለጫው ከዪክሬን የሚደረግላቸው ድጋፍ የምግብ የነዳጅና የሕክምና ብቻ እንደሆነ አስምሮበታል።

ዴኒስ ካፑስቲን ሩሲያ አንድ ወጥ ብሔር ያላት ከፑቲን ተጽእኖ ነጻ የሆነች ታላቅ አገር መፍጠር እንፈልጋለን ብሏል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እነዚህ ሸማቂ ቡድኖች ተጠቅመውበታል ያለውን አሜሪካ ሠራሽ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ፎቶ አጋርቷል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከዚህ በኋላ በነዚህ ቡድኖች ፈርጣማ ክንዱን እንደሚያሳርፍ ዝቷል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ሩሲያ ላይ እጃቸውን እያስገቡ ያሉ ምዕራባዊያን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

እነዚህ ታጣቂዎች ቤልጎሮድ ግዛትን በቅርቡ ከሩሲያ ነጻ እናደርጋለን ሲሉ ይዝታሉ።