
25 ግንቦት 2023, 12:24 EAT
ባለፉት 20 መታት በአፍሪካ የቱርክ ተጽዕኖ እጅጉን እያደገ መጥቷል።
በመጪው ቅዳሜ ማንም አሸነፈ ማን ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ወዴትኛው ምዕራፍ መውሰድ እንዳለበት ማጤን ይጠበቅበታል።
ከሁለት ዐሥርታት በፊት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን መጀመርያ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን በኋላ ደግሞ የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ በአፍሪካ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየት ጀምረዋል።
ኤርዶዋን በአፍሪካ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እድሎችን ተመለከቱ።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ዳግም የሚመረጡ ከሆነ አህጉሪቱ እና አንካራ ግንኙነታቸውን ዳግም ያጠናክራሉ።
ተቀናቃኛቸው የሆኑት የሪፐብሊካን ፒፕልስ ፓርቲ መሪ ከማል ኪሊችዳሮሉ፣ ዓይናቸውን የጣሉት አውሮጳ እና ምዕራቡ ላይ ነው።
ልባቸው ለአፍሪካም ብዙም ድንጉጥ አይመስልም።
“ ከማል ኪሊችዳሮሉ ከምዕራቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። አገሪቱ የአውሮጳ አባል አገር ለመሆን የምታደረገውን ጥረትም ዳግም ለማስጀመር ቃል ገብተዋል” ይላል በአንካራ የሄርያት ዴይሊ ኒውስ ቢሮ ኃላፊ እና የቱርክ ውጪ ጉዳይ ፖሊስ ኤክስፐርት የሆነው ሴርካን ዲሚትሪስ።
“በቃለ መጠይቃቸው ላይ፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲውን በሚመለከት 180 ዲግሪ መዞር እንደሚኖር ተናግረዋል። ነገር ግን ይህ ለውጥ ከቁልፍ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት ተጽዕኖ እንደሚኖረው ከመግለጽ ተቆጥበዋል”
ይኹን አንጂ የቢቢሲ ተርኪሽ አገልግሎት ባልደረባ የሆነው ኢሴ ጎክሴዴፍ በአህጉሪቱላይ ያላት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንደገና መስመር ለማስያዝ ጊዜ እንደሚጠይቅ ይናገራል።
ስለዚህ ይህ አዲሱ ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ በመሆኑ በፍጥነት ለውጥ ያስከትላል ብሎ መጠበቅ አይቻልም ይላል።
- በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሠፈራቸውን የመሠረቱ ኃያላን አገራት17 ግንቦት 2023
- የቤት ውስጥ ጥቃትን አሸንፋ ዓለም አቀፍ እውቅናን የተቀዳጀችው ቲና ተርነር25 ግንቦት 2023
- በቱርክ ምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ዕጩ ባለመኖሩ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሊደረግ ነው15 ግንቦት 2023
የአፍሪካ እና የቱርክ ግንኙነት መነሾ
በአፍሪካ እና በቱርክ መካከል ያለው ትብብር የጀመረው በኤርዶዋን የጠቅላይ ሚኒስትርነት የሥልጣን ዘመን በ2003 እኤአ ነው።
ኤርዶዋን ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም በአህጉሪቱ ገበያ ላይ አዩ።
“በ2000ዎቹ መጀመርያ ላይ የቱርክ ምጣኔ ሃብት ተከታታይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ ነበር። ስለዚህም አዲስ ገበያ መፈለግ ጀመረ” ይላል የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ኤክስፐርቱ ዲሚትሪስ።
“ ከ50 በላይ አገራት ጋር መልከ ብዙ የሆነ ገበያ ተፈጠረ፤ እንዲሁም ከ1.2 ቢሊዮን ሰዎች በውጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ድጋፍ ተደረገላቸው።”
እንደ ቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት መረጃ ከ2003 እስከ 2021 ባሉት ዓመታት ብቻ ቱርክ ከአህጉሪቱ ጋር ያላት ንግድ ከ5.4 ቢሊዮን ወደ 34.5 ቢሊዮን ተመነደገ።
ቱርኮች ከአህጉሪቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት የመመዝበር አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
በ2013 ኤርዶዋን ጋቦንን በሚጎበኙበት ወቅትም “አፍሪካ ለአፍሪካውያን ትገባለች፤ እኛ እዚህ ያለነው ለወርቃችሁ አይደለም” ብለው ነበር።

ወታደራዊ ፍላጎት
ለአንካራ ከአፍሪካ አገራት ጋር የሚደረገው የጦር መሣርያ ስምምነት ወይንም አንዳንዶች አንደሚጠሩት “የድሮን ዲፕሎማሲ” የውጪ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ንግዶች መካከል አንዱ ነው።
በሊቢያ፣ አርሜንያ እና ዩክሬን ውጤታማነታቸው ከታየ ወዲህ ‘ባይራክታር ቲቢ-2’ ድሮኖች በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሱ ጂሀዲስቶችን ዒላማ ለማድረግ ዋነኛ ጦር መሣርያ ሆነዋል።
በመጋቢት ወር በማሊ ዋና ከተማ ባማኮ በርካታ ድሮኖች ደርሰዋል።
የተወሰኑ የቱርክ ዲፕሎማቶች እና የማሊ ወታደራዊ አመራር ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ፣በተገኙበት የማሊ መከላከያ ሚኒስትር አዲስ የመጡትን መሳርያዎች ሲቀበሉ፣ “ድጋፉ የአየር ጥቃቱን የበለጠ ዒላማውን የጠበቀ ያደርገዋል” ብለዋል።
ከማሊ በተጨማሪ ቱርክ ለቡርኪናፋሶ፣ ቶጎ፣ ኒጀር በአገሮቻቸው የእስላማዊ ታጣቂዎችን ለመዋጋት ለሚያደርገት ትግል የድሮን ሽያጭ አከናውናለች።
ከዚህ ባሻገር እስካሁን ድረስ እስላማዊ ታጣቂዎች ሳይታይባት ቆይታ የነበረቸው እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቃቶችን ማስተናገድ ከጀመረችው ከቤኒን ጋር በንግግር ላይ ትገኛለች።
በአህጉሪቱን የድሮን ገበያ ቻይና በበላይነት ብትይዘውም ቱርክ ግን ኪስ በማይጎዳ ዋጋ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ታቀርባለች።
ቱርክ ከድሮን በተጨማሪ ሌሎች ጦር መሳርያዎችንም ለአፍሪካ አገራት ታቀርባለች።
በአጠቃላይ 30 አፍሪካ አገራት ከደኅንነት ጋር የተያያዘ ስምምነት ከቱርክ ጋር አድርገዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 21ዱ በ2017 የተፈረሙ መሆናቸውን የጀርመኑ የዓለም አቀፍ እና የጸጥታ ጉዳዮች ኢንስትቲዩት መረጃ ያሳያል።

የቱርክ ዲፕሎማሲ እንዴት መልኩን ቀየረ
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ከወታደራዊ እና ንግድ ግንኙነቶች ውጪ፣ የቱርክ እና አፍሪካ ግንኙነትን መሠረት በማስያዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በ2005 ቱርክ በአፍሪካ ኅብረት የታዛቢነት መቀመጫ አግኝታለች።
ይህ የሆነው ቱርክ የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ አጋር ከመሆኗ ሶስት ዓመት ቀደም ብሎ ነው።
ቱርክ ከ2014 ጀምሮ 50 ይፋዊ የስራ ጉብኝቶችን በአፍሪካ አገራት ማካሄዷን ትናገራለች።
ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ሴኔጋልን አራት ጊዜ ጎብኝተዋል፣ ልክ ቻይና እና ጀርመንን እንደጎበኙት ሁሉ ማለት ነው።
በሚሄዱበት ሁሉ የንግድ ልዑካን አብረው ይጓዛሉ።
ይህም ቁልፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለቱርክ ኩባንያዎች እንዲሰጥ አድርጓል።
ከእነዚህም መካከል የዳካር ኦሎምፒክ የመዋኛ ገንዳ ወይንም በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የሆነው የሩዋንዳ ኪጋሊ ስታድየም ይገኙበታል።
የአፍሪካ መሪዎችም ቢሆኑ የቱርክ አፍሪካ ጉባኤን ቀርተው አያውቁም።
ቱርክ በአፍሪካ 44 ኤምባሲዎች ሲኖራት አሜሪካ 49፣ ፈረንሳይ 46፣ ቻይና 53 አሏቸው።
ይህም ቱርክ በዲምሎማሲው ረገድ በአፍሪካ ጠንካራ መሰረት መጣሏን ማሳያ ይሆናል።
ቱርክ ለአፍሪካ ሌላ ምን ልትሰጥ ትችላለች?
ቱርክ በአፍሪካ ያላትን የእጅ አዙር ተጽዕኖ ለማጠናከር ትፈልጋለች።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ ይፋ የሆነው የቲአርቲ አፍሪካ በይፋ ስራ መጀመር ነው።
የቱርክ የሕዝብ መገናኛ ብዙኀን የሆነው ቲአርቲ በፈረንሳይኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ስዋሂሊ እና ሀውሳ ቋንቋዎች ስርጭቱን ጀምሯል።
ከዚህ ሁሉ ይልቅ ግን የቱርክ የእጅ አዙር ተጽዕኖ የሚመጣው በሶፕ ኦፔራዎቿ ነው።
የቱርክ ተከታታይ ድራማዎች ከኢትዮጵያ እስከ ሴኔጋል ብዙዎች የሚወዱት እና የሚከታተሉት ድራማ ነው።
እምብዛም የቱርክ ተሳትፎ ሲነገርበት የማይሰማው ግን በኃይል አቅርቦት ላይ ያላት ተሳትፎ ነው።
የፕሬዝዳንቷን ጉብኝት ተከትሎ የቱርክ ኩባንያ የሆነው ካርፓወርሺፕ፣ ለበርካታ ምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት የኃይል አቅርቦት ላይ ለመስራት ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
ኤርዶዋን የሚያሸንፉ ከሆነ ይህንን የተጀመረ ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራሉ።
በተቃራኒው ተቀናቃኛቸው፣ ከማል ኪሊችዳሮግሉ ካሸነፉ ደግሞ አፍሪካ በቱርክ ፊት ያላት ሞገስ እንደ ቀድሞ ዓመታት አይሆንም።
ነገር ግን እስካሁን የተጀመረውን እና መሰረት ያዘውን ግንኙነትን የሚጎዳ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ አይጠበቅም።