
ከ 4 ሰአት በፊት
በደቡብ አሜሪካዋ አገር ጉያና ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ተነስቶ ለ19 ተማሪዎች ሞት ምክንያት የሆነው የእሳት አደጋ በአንዲት ተማሪ ሆን ተብሎ የተቀሰቀሰ መሆኑን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ባለፈው ሰኞ በተማሪዎች ማደሪያ ሕንጻ ላይ በተነሳው የእሳት አደጋ ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ሰለባዎቹ ከአደጋው እንዳያመልጡ በር ተዘግቶባቸው እንደነበር ተገልጿል።
እሳቱን ያስነሳችው ተማሪ በትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች የሞባይል ስልኳን በመቀማቷ ተበሳጭታ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ እሷም በአደጋው ጉዳት ደርሶባት ሆስፒታል ገብታለች።
የአሶሺየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ተማሪዋ በዕድሜ ከሚበልጣት ግለሰብ ጋር ግንኙነት በመጀመሯ በትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ስትቀጣ ጥቃት እንደምትፈጽም ስትዝት ነበር ተብላ ተከሳለች።
ተማሪዋ ወደ 20 ለሚጠጉ ሰዎች ሞት እና ከባድ ውድመት ምክንያት የሆነውን የእሳት አደጋ ማስነሳቷን ያመነች ሲሆን፣ ባለሥልጣናትም ተማሪዋ ላይ ክስ መመስረት እንዳለባቸው ለመወሰን የባለሙያዎች ምክር እየጠየቁ ነው።
- ከፑቲን ‘ምግብ አብሳይነት’ ተነስቶ በዩክሬኑ ጦርነት ውስጥ ቁልፍ ሰው የሆነው ግለሰብከ 5 ሰአት በፊት
- ‘ቲክቶከሯ’ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾችን ላይ ለፈጸመችው ጥፋት ፍርድ ቤት ቀረበችከ 5 ሰአት በፊት
- ሜሰን ማውንት ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ማዲሰን ወደ አርሰናል?25 ግንቦት 2023
እሳቱ የተነሳው ከተማሪዎች መታጠቢያ ቤት እንደነበረ እና ወዲያውኑም በከፊል ከእንጨት ወደ ተሰራው እና 57 ተማሪዎች ወደ ሚያድሩበት መኖሪያ ህንጻ ተሸጋግሮ ነው ጉዳት ያስከተለው።
የተማሪዎቹ የመኝታ ክፍል አስተዳዳሪ የሆነችው እና እሷም በአደጋው የአምስት ዓመት ልጇን ያጣችው ግለሰብ፣ በአደጋው በመደናጋጧ የበሮቹን ቁልፍ ልታገኛቸው ስላልቻለች እሳቱ በተማሪዎቹ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።
እኩለ ሌሊት ላይ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ወቅት ተማሪዎቹን ለማዳን በሮችን ለመክፈት ባለመቻሉ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ግድግዳ በማፍረስ ወደ ውስጥ መዝለቃቸው ተዘግቧል።
እሳቱን ለማጥፋት በመጀመሪያ ላይ የተደረገው ጥረት በመጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት አስቸጋሪ ሆኖባቸው እንደነበር የእሳት አደጋ ሠራተኞች ገልጸዋል።
በእሳቱ ለህልፈት ከተዳረጉት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ከአገሪቱ ቀደምት ማኅበረሰቦች የመጡ ሲሆኑ፣ በርካቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በማዕከላዊ የጉያና ግዛት ውስጥ በተከሰተው አደጋ ከተጎዱ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት ወደ ዋና ከተማዋ ጆርጅ ታውን ለህክምና ሲወሰዱ፣ አብዛኞቹ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የደረሰው የእሳት አደጋ አስከፊ ስለነበረ በአደጋው ከሞቱት መካከል የተወሰኑትን ለመለየት የዘረ መል ምርመራ አስፈልጓል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢርፋን አሊ በተማሪዎቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት “ከባድ አደጋ” ሲሉ ገልጸውታል።