
ከ 4 ሰአት በፊት
በሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወቅት ከሁለት ሺህ በላይ በሚሆኑ ሰዎች ሞት ውስጥ ተሳታፊ ነበረ በሚል ሲፈለግ የቆየው ተጠርጣሪ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተያዘ።
በሚቀጥለው ዓመት 30 ዓመት በሚሞላው እና በፈረንጆቹ 1994 በተካሄደው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው ከሚፈለጉ አራት ግለሰቦች መካከል አንዱ መያዙን የተባበሩት መንግሥታት ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ፉልጌንስ ካይሼማ ባለፈው ረቡዕ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን መርማሪዎች ገልጠዋል።
ግለሰቦች የፍርድ ሂደቱን ሩዋንዳ ውስጥ ይከታተላል።
ቀድሞ የፖሊስ አባል የነበረው ተጠርጣሪው ከ2 ሺህ በላይ የቱትሲዎች አንድ ቤተ-እምነት ውስጥ እንዲገደሉ አስተዋፅዖ አድርጎ ነበር ይባላል።
በወቅቱ ሕፃናት እና ሴቶችን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ቱትሲዎች ቤተ-እምነት ውስጥ ተሸሽገው ነበር።
በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከ800 ሺህ በላይ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች ተገድለዋል።
የክስ መዝገቡ እንደሚያሳየው ተጠርጣሪው ግድያውን ከማቀድም በላይ በንያንጌ ቤተ-ክርስቲያን ተጠልለው የነበሩ ሰዎችን በመግደል ተሳትፏል።
በፈረንጆቹ 1962 የተወለደው ተጠርጣሪ እና ሌሎቹ ተባባሪዎች ሰዎች ተጠልለውበት የነበረውን ቤተ-ክርስቲያን ለማቃጠል ሞክረዋል።
- ‘የሆቴል ሩዋንዳ’ፊልም ጀግና ከእስር ተፈቱ25 መጋቢት 2023
- የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ‘አቀነባባሪ’ የፍርድ ሂደት በጊዜያዊነት ቆመ11 መጋቢት 2023
- የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ ፍለጋ በመቃብሩ ውስጥ ተጠናቀቀ13 ግንቦት 2022
ይህ አልሳካ ሲላቸው ቤተ-ክርስቲያኑን በማፈራረስ ብዙዎችን እንዲገደሉ እና እንዲቀበሩ አድርገዋል።
የሰዎቹም አስከሬን በጅምላ መቃብር እንዲቀበር እንደተደረገ የክስ መዝገቡ ያሳያል።
ዘ ሄግ የሚገኘው መሰል ጉዳዮችን የሚመለከት ችሎት ባወጣው መግለጫ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር በመዋሉ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አንድ ልዩ ግብረ-ኃይል ግለሰቡን ዌስተርን ኬፕ ግዛት ከሚገኝ የወይን ማሳ ውስጥ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው አሳውቋል።
ተጠርጣሪው ዶናትየን የተሰኘ ሐሰተኛ ስም ተጠቅሞ ከፖሊስ ፍለጋ በመሸሽ ይኖር ነበር።
የፖሊስ መግለጫ እንደሚጠቁመው ተጠርጣሪው መጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ፍርድ ቤት ይቀርብና ቀጥሎ ወደ ሩዋንዳ እንዲወሰድ ይደረጋል።
የግለሰቡን መያዝ ተከትሎ የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት ዮላንዴ ማኮሎ “በስተመጨረሻም” ሲሉ ትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።
መቀመጫውን ታንዛኒያ ያደረገው አይሲቲአር የተሰኘው ተቋም ከ60 በላይ የዘር ማጥፋቱ አስተባባሪዎች ላይ ከዚህ ቀደም ፍርድ መስጠቱ ይታወሳል።
ይህ ተቋም ከተዘጋ በኋላ ነው ዘ ሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት የተቋቋመው። ነገር ግን የካይሼማን ጉዳይ ጨምሮ ሌሎች የፍርድ ሂደቶች ሩዋንዳ ውስጥ ይካሄዳሉ።