ኢላን መስከ

ከ 2 ሰአት በፊት

ኒውራሊንክ የተባለው በሰው አንጎል ውስጥ ‘ቺፕ’ የሚቀብረው የኢላን መስክ ድርጅት በሰው ልጅ ላይ ሙከራ እንዲያደርግ ተፈቀደለት።

የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳዳር ባለሥልጣን (ኤፍዲኤ) ኒውራሊንክ የተሰኘው ተቋም ሙከራውን የሰው ልጅ ላይ እንዲያደርግ ፈቅዷል።

የቢሊየነሩ ኩባንያ ኮምፒውተር እና የሰው ልጅ አንጎልን በማገናኘት የሰዎችን የማየት አቅም እና እንቅስቃሴ ማገዝ ይፈልጋል።

ኒውራሊንግ እንዳለው ወዲያውኑ ሰዎች ላይ ሙከራ የማድረግ ሥራ አይጀምርም። ይህ ማለት ኢላን እንደተመኘው ሳይሆን በሰዎች ላይ ሙከራ ለማድረግ ጊዜ ይወስዳል።

ፈቃድ የሰጠው የአሜሪካው ተቆጣጣሪ ድትጅት እስካሁን ስለጉዳዩ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ከዚህ ቀደም ኒውራሊንክ ከኤፍዲኤ ፈቃድ ለማግኘት ሞክሮ የደኅንነት ጉዳዮች አሳሳቢ ሆነው በመገኘታቸው ተከልክሎ ነበር።

ባለፈው መጋቢት ሮይተርስ የዜና ወኪል በርካታ የቀድሞ እና የአሁን የኒውራሊንክ ሠራተኞችን አጣቅሶ ፈቃድ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ዘግቦ ነበር።

ኒውራሊንክ፤ ‘ማይክሮቺፕ’ ተጠቅሞ ሰውነታቸው የማይታዘዛቸውን (ፓራላይዝ) እና ዐይነ-ስውራንን መርዳት ያልማል።

አልፎም አንዳንድ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ኮምፒውተር እና ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲጠቀሙ ለማድረግ አመቺ ሆኑታን ይፈጥራል ተብሏል።

ዝንጀሮዎች ላይ ሙከራ የተደረገባቸው ጥቃቅኖቹ ቺፖች መልዕክት ከአእምሮ ተቀብለው በብሉቱዝ አማካይነት መረጃ ያሠራጫሉ።

መስክ፤ ከዚህ ቀደም ይህ ቴክኖሎጂ የሰው ልጅ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ሊተካ ይችላል የሚለውን ስጋት ያቀላል የሚል አስተያየት ሰጥቶ ነበር።

ሐሙስ ዕለት ዜናውን ትዊትር ላይ የለጠፈው ኒውራሊንክ “የሰው ልጅን ለማገዝ አንድ እርምጃ ወደፊት ተጉዘናል” ብሏል።

ተቋሙ በቅርቡ የሰው ልጅ ላይ ሙከራ ለማድረግ “ተሳታፊዎችን” መመዝገብ እንደሚጀምር አሰውቋል።

የኒውራሊንክ ድረ-ገጽ “ደኅንነት፣ ተደራሽነት እና አስተማማኝ” የሆነ ሥራ እንደሚሠራ ቃል ገብቶ ጥናቱን በጥንቃቄ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ግን አእምሮ ውስጥ ቺፕ መቅበር በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ እና ከባድ ጥናት የሚጠይቅ ነው ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

አልፎም ቴክኖሎጂው በሰፊው ከመሠራጨቱ በፊት ቴክኒካዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ጎኑ መቃኘት አለበት ይላሉ።

በፈረንጆቹ 2016 ኢላን መስክ በተባባሪነት ያቋቋመው ኒውራሊንክ በተደጋጋሚ ይህን ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ለማዋል ቢሻም ዕቅዱን ሲገፋው ቆይቷል።

የመጀመሪያ ዕቅዱ የነበረው በ2020 የሰው ልጅ አእምሮ ውስት ቺፕ መቅበር ነበር። ቀጥሎ ደግሞ በ2022 ይህን ለማድረግ ቃል ገባ።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት የእንስሳት ደኅንነትን አደጋ ላይ ጥሏል በሚል በተከፈተበት ምርመራ ምክንያት ዕቅዱን እንደገና አዘገየ።

የኒውራሊንክ ፈቃድ ማግኘት ዜና የመጣው የስዊትዘርላንድ አጥኚዎች አእምሮ ላይ በተሳካ ሁኔታ ኮምፒውተር ከቀበሩ በኋላ ነው።

በዚህም ሰውነቱ የማይታዘዝለት አንድ የኔዘርላንድስ ዜጋ ጭንቅላቱ ውስጥ በተቀበረለት ቴክኖሎጂ አማካይነት ስለመራመድ በማሰብ ብቻ መራመድ መቻሉ ተነግሯል።