
ከ 5 ሰአት በፊት
ኦርላ ሜሊሳ የተባለች የቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ቲክቶክ ተሳታፊ፣ በታዋቂ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾች ላይ ለፈጠረችው ጫና ፍርድ ቤት ቀረበች።
ወጣቷ ‘ቲክቶከር’ ለፍርድ ቤቱ ሁለት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾችን መሰለሏን እንዲሁም ሦስተኛ ተጫዋች መተናኮሷን አመናለች።
ይህች የ21 ዓመቷ ኦርላ ሜሊሳ ስሎን ከቼልሲው ሜሰን ማውንት ጋር የፍቅር ግንኙነት እንደነበራት ተነሯል።
ነገር ግን ከተለያዩ በኋላ ለአራት ወራት ያክል በድብቅ ትከታተለው እና በፅሑፍ መልዕክት ታጨናንቀው እንደነበር አምናለች።
አልፎም የሜሰን ማውንት የቀድሞው የቡድን አጋር የነበረውን የ21 ዓመቱ ቢሊ ጊልሞርን ትከታተለው ነበር ተብሏል።
በዚህ ያልተመለሰችው ‘ቲክቶከር’ የ26 ዓመቱ የቼልሲ ተከላካይ ቤን ቺልዌልን መተናኮሷን ገልጻለች።
ቢሊ ጊልሞር ተከሳሿ የምትልከው መልዕክት በሕይወቴ ላይ “ተፅዕኖ አሳድሮብኛል” ሲል ለችሎቱ ተናግሯል።
የዌስት ሚኒስቴር ፍርድ ቤት እንደሰማው ማውንት እና ኦርላ፤ ቤን ቼልዌል ቤት ኅዳር 2020 ከተገናኙ በኋላ አብረው አድረዋል።
ዐቃቤ ሕግ ጄሰን ሲታል እንዳሉት ማውንት “የፍቅር ግንኙነቱን ከመቋጨቱ” በፊት ለስድስት ወራት ያክል አብረው ዘልቀዋል።
- በ5 የዓለም ዋንጫዎች በመሳተፍ የመጀመሪያ የሆኑት እግርኳስ ተጫዋች በ93 አመታቸው አረፉ10 ግንቦት 2023
- ኢራን የተቃውሞ ሰልፍ ደግፏል ባለችው ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቿ ላይ የጉዞ እገዳ ጣለች6 ግንቦት 2023
ተጫዋቹ ከኦርላ የሚደርሰው የፅሑፍ መልዕክት ከልክ በላይ ሲሆንበት ስልክ ቁጥሯን ‘ጥቁር መዝገብ’ ውስጥ እንደከተተው [ብሎክ እንዳረጋት] ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል።
“ከዚያ በኋላ ከማያውቀው ቁጥር በርካታ የፅሑፍ መልዕክቶች ይደርሱት ነበር። አንዱን ቁጥር ‘ብሎክ’ ሲያደርግ በሌላ ቁጥር መልዕክት ይደርሰዋል” ይላል የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ።
ፍርድ ቤቱ እንዳደመጠው ተከሳሿ በአጠቃላይ 21 የስልክ ቁጥሮችን ተጠቅማ ሜሰን ማውንትን ለማግኘት ሞክራለች።
ዐቃቤ ሕጉ እንዳሉት ሜሰን ማውንት ግለሰቧ “ከእሱ አንድ ዓይነት አባዜ እንደያዛት ከመጠርጠርም በላይ ምን ዓይነት አደጋ ልታመጣ እንደምትችል ባለማወቁ ስጋት ውስጥ ገብቷል።”
ተጫዋቹ ባወጣው መግለጫ ግለሰቧ “ወደ ሥልጠና ቦታ ልትመጣ ትችላለች” የሚል ስጋት እንደነበረው ግልጿል።
ፍርዱ ቤቱ ጨምሮም እንደተመለከተው ቤን ቺልዌልን ጨምሮ ሌሎች የሜሰን ማውንት የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞችም መልዕክት ይደርሳቸው ነበር።
ባለፈው መስከረም ከቼልሲ ወደ ብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢዮን የተዘዋወረው ጊልሞር የተከሳሿ መልዕክት “ጫና” ያሳድረበት ነበር።
“እንቅልፍ መተኛት ተስኖኝ የእንቅልድ መድኃኒት መውሰድ ጀምሬ ነበር” ብሏል።
የኤክስተር ከተማ ነዋሪዋ ኦርላ የቀረበባትን ክስ ያመነች ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከመስከረም እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ጊልሞር ላይ “ከባድ ጭንቀት” እንዳስተከለች ተናግራለች።
አልፎም ሜሰን ማውንትን ባለፈው ዓመት ከሰኔ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ስትከታተለው እና ጫና ስታሳድርበት እንደነበር እንዲሁም ቤን ቺልዌን እንደተተናኮሰች አምናለች።
ተከሳሿ ለጊዜ በዋስ የተለቀቀች ሲሆን፣ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ የቅጣት ውሳኔ ይሰጣል።