
26 ግንቦት 2023, 12:30 EAT
አንድ ግለሰብ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ሊያርፍ የተቃረበ አየር ላይ የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላንን የአደጋ ጊዜ በር በመክፈቱ ምክንያት በፖሊስ በቁጥጥር ስር ዋለ።
ግለሰቡ ኤሺያን ኤርላይንስ የተባለ አየር መንገድ ንብረት በሆነው የመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍሮ በመጓዝ ላይ ሳለ ነው በድንገት የአደጋ ጊዜ መውጫውን በር የከፈተው።
ዛሬ አርብ 194 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን በሩ እንደተከፈተ ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም ያረፈ ሲሆን፣ በመንገደኞች ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም።
ነገር ግን በተከፈተው በር ምክንያት በአውሮፕላኑ ውስጥ በተፈጠረ የአየር ግፊት መዛባት የተነሳ ቢያንስ ስድስት ተሳፋሪዎች የመተንፈስ ችግር ግጥሟቸው ስለነበረ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የአውሮፕላኑን በር ከፍቷል የተባለው በ30ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ አውሮፕላኑ ካረፈ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን ዮንሃፕ የተባለው የደቡብ ኮሪያ ዜና ወኪል ዘግቧል።
- በሰው አንጎል ውስጥ ‘ቺፕ’ የሚቀብረው የኢላን መስክ ኩባንያ በሰው ላይ ሙከራ ሊያደርግ ነው26 ግንቦት 2023
- ሞባይል የተነጠቀችው ተማሪ ትምህርት ቤቷ ውስጥ ባስነሳችው እሳት 19 ሰዎች ሞቱ26 ግንቦት 2023
- በሺዎች ሞት ሲፈለግ የነበረው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ተጠርጣሪ ከ30 ዓመት በኋላ ተያዘ26 ግንቦት 2023

አንድ አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ የአይን ምስክር እንደተናገረው አውሮፕላኑ ለማረፍ እየተዘጋጀ ስለነበረ አስተናጋጆቹ ግለሰቡን በሩን ከመክፈት ሊከላከሉት አልቻሉም።
በተጨማሪም ግለሰቡ በሩን ከከፈተ በኋላ ከአውሮፕላኑ ዘሎ ለመውጣት ሞክሮ ነበር ተብሏል።
የአውሮፕላኑ በር ከተከፈተ በኋላ በተሳፋሪዎች መካከል ከባድ ድንጋጤ እና ሽብር ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ አንድ ተሳፋሪ “አውሮፕላኑ የሚፈነዳ መስሎ ስለተሰማን እዚያው የምሞት ነበር የመሰለኝ” ብሏል።
አውሮፕላኑ ሁለት መቶ የሚጠጉ ሰዎችን አሳፍሮ የደቡብ ኮሪያ ትልቋ ደሴት ከሆነችው ጄጁ የተነሳው ዛሬ አርብ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት ላይ ነበር።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ግለሰቡ የአውሮፕላኑን በር የከፈተው ወደ መዳረሻው ሲቃረብ አየር ላይ ሳለ ነበር።
አንድ በአውሮፕላኑ ተሳፍሮ የነበረ መንገደኛ በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራው ቪዲዮ ላይ፣ በአውሮፕላኑ አንድ ወገን የተከፈተው በር ክፍተት እና ከባድ ነፋስ ከተከፈተው በር አቅራቢያ የነበሩ ወንበሮችን በኃይል ሲነቀንቃቸው ታይቷል።
በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል በሳምንቱ ማብቂያ በሚካሄድ የስፖርት ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚጓዙ በርካታ ተማሪ ልጆች እንደነበሩ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከልጆቹ መካከል የአንዳቸው ወላጅ ለዮንሃፕ ዜና ወኪል እንደተረናገሩት በክስተቱ “ልጆቹ በጣም ፈርተው እየተንቀጠቀጡ እና እያለቀሱ ነበር።”
አየር መንገዱ ኤሺያን ኤርላይንስ ከክስተቱ በኋላ ፖሊስ ሙሉ ምርመራ መጀመሩን አሳውቋል።