
26 ግንቦት 2023
ዛሬ አርብ ከጁምዓ ሶላት በኋላ ፖሊስ ተቀሰቀሰ ባለው ረብሻ እና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ፖሊስ እንዳለው በክስተቱ በርካታ የፀጥታ ኃይል አባላት እና ሌሎችም የቆሰሉ ሲሆን፣ ይህንን ረብሻ ቀስቅሰዋል የተባሉ ከ110 በላይ ተጠርጣሪዎችን መያዙንም ገልጿል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለው የሸገር ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ነው የተባለው መስጂዶችን የማፍረስ ድርጊት እንዲቆም የእምነቱ መሪዎች ለመንግሥት ጥሪ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ከአርብ ጸሎት በኋላ በተለያዩ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ መስጂዶች ተቃውሞዎች ተሰምተዋል።
በዚህ በጎዳናዎች ላይ የመስጂዶች ፈረሳን የተቃወሙ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ተቃውሟቸውን ባሰሙበት ወቅት ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት መፈጠሩን ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፣ በተለይ መርካቶ አካባቢ ውጥረት እንደነበር ቢቢሲ ያናገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
ፖሊስ ምሽት ላይ ባወጣው መግለጫ ላይም አርብ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም. ረፋድ በአዲስ አበባ ከተማ በታላቁ የአንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ “ረብሻ እና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት” ማለፉን እና በፖሊስ አባላት ላይም ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ፖሊስ ጨምሮም ሕይወታቸው ያለፈው ሁለቱ ሰዎች መርካቶ ጋዝ ተራ በሚባለው ስፍራ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ መሞታቸውን አመልከቷል።
ፖሊስ ተከሰተ ያለውን ብጥብጥ በመምራት እና በማስተባበር እንዲሁም ዋነኛ ተሳትፎ ነበራቸው ያላቸውን 114 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ማዋሉንም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በዚህ ክስተት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ አራት ግለሰቦች ጉዳት ሲደርስባቸው፣ “37 የፖሊስ አመራር እና አባላት እንዲሁም 15 ሌሎች የፀጥታ ኃይል አጋዦች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት” እንደደረሰባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ጨምሮም በዚህ ክስተት የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሁለት አውቶቡሶች ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
የተከሰተው “ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢዎቹ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን” በመጥቀስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋነኑ መረጃዎች ተሰራጭተዋል ብሎ ፖሊስ ተችቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአካባቢው የሚኖሩ እና የሚሰሩ ግለሰቦች የተከሰተው ሁኔታ አሳሳቢ እንደነበር እና ለረጅም ሰዓታት ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም የተነሳ የትራንስፖርት ችግር እንደበር እና የፀጥታ ኃይሎች አካባቢዎቹን ከተቆጣጠሩ በኋላ እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው ነበር ብለዋል።
- የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሸገር ከተማ ቢያንስ ሰባት መስጊዶች መፍረሳቸውን ገለጸ20 ግንቦት 2023
- ከሰሞኑ ቤቷ የፈረሰባት የ20 ቀኗ አራስ እና የሸገር ከተማ ነዋሪዎች እሮሮ25 የካቲት 2023
- ሕገ ወጥ የሚባሉት ቤቶች የትኞቹ ናቸው? ነዋሪዎችስ ምን መብት አላቸው?7 ሚያዚያ 2023
የኦሮሚያ ክልል አዲስ በመሠረተው የሸገር ከተማ ውስጥ አስካሁን ድረስ ቢያንስ ሰባት የሚደርሱ መስጊዶች መፍረሳቸውን የኢትዮጵያ አስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሒም ቱፋ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በከተማው ውስጥ ከመስጂዶች ባሻገር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ የተባሉ መኖሪያ ቤቶች መፈረሳቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ባለፉት ቀናት የመስጂዶችን መፍረስ በመቃወም የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ለመንግሥት ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣት እንዳለባቸው ጥሪ የሚያቀርቡ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሲዘዋወሩ ነበር።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው ሁኔታም የዚሁ አካል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ፖሊስም በመግለጫው “በከተማዋ ውስጥ በሕዝበ ሙስሊሙም ሆነ በዕምነት ተቋሙ ላይ የተፈጠረ ችግር ሳይኖር በሌሎች ቦታዎች ላይ መስጊድ ፈርሷል በሚል ምክንያት ሕገ-ወጥ ሰልፍ በማድረግ ሁከት እና ብጥብጥ በማስነሳት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
አክሎም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አቅደው ተንቀሳቅሰዋል ባላቸው ግለሰቦች ላይ የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዱት እርምጃ ተጠናክሮ እንሚቀጥል ገልጿል።