May 27, 2023 – BBC Amharic

ናስር አህመድ ለአስር ዓመት ያህል በዚህ የሙያ መስክ ላይ ቆይቶ፣ ዋሻዎችን ተመራምሮ የደረሰብትን ግኝት በመጽሐፍ መልክ ሰንዶ አሳትሞታል።

ከ 8 ሰአት በፊት

ናስር አሕመድ ብዙዎች በማያውቁት የሙያ ዘርፍ ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል።

ስፒሊዮሎጂ (Speleology) ነው ያጠናው።

ይህ የጥናት ዘርፍ የዋሻ ምርምር እና አሰሳዎች ላይ የሚያተኩር ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ብዙም የተለመደ ሙያ አይደለም።

ናስር ግን በዋሻዎች ፍቅር ልቡ ሸፍቷል። ፍቅሩም ዋጋውን ከፍሎታል፤ ዋሻ ከማጥናት፣ ከማሰስ እና ከመመዝገብ አልፎ፣ በስሙ ዋሻ ተሰይሞለታል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የዋሻ ተማራማሪ ነኝ የሚለው ናስር አህመድ ማን ነው?

ናስር ማን ነው?

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ውስጥ በምትገኛው ኮምቦልቻ ወረዳ ነው ተወልዶ ያደገው።

“ከሕጻንነቴ ጀምሮ ለናሽናል ጂኦግራፊ ትልቅ ፍቅር አለኝ እከታተልም ነበር” የሚለው ናስር ለዚህ ሙያ ያለው ፍቅር የጀመረው ትምህርት ቤት ሆኖ ባጋጠመው አንድ ክስተት ነው።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ አገርህን (ባሕልህን) እወቅ የሚባል ክበብ ውስጥ ይሳተፍ ነበር።

መምህራቸው ‘ጎዳ ወንጂ’ ወደሚባል ዋሻ ወሰዳቸው።

የዚያን ቀን ሁሉም ልጆች ወደ ዋሻው መግቢያ እየተመለከቱ ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባትን ፈሩ።

“እኔ ግን ምንም ፍርሃት ሳይኖርብኝ ገባሁኝ። የዋሻ ፍቅር ያደረብኝ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው” ይላል ናስር።

በልጅነት ልቡ ላይ ዋሻ ፈልጎ የማግኘት፣ የዋሻን ሆድ በርብሮ በውስጡ ያለውን የማወቅ ጉጉት፣ የአገሪቱን ዋሻዎች አንድ በአንድ ቆጥሮ እና መዝግቦ የማስቀመጥ ህልሙ ያኔ ተጸነሰ።

በእርግጥ የናስር ልብ ከዋሻ ጋር ይክነፍ እንጂ ቤተሰቡ ግን ለእርሱ የሚያስበው ሌላ ነው።

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በቤተሰቦቹ ፍላጎት መሠረት የሕክምና ሙያ ውስጥ በመግባት ተማረ።

ናስር ነጭ ጋወን ለብሶ ሕሙማንን በማከም የሚገኝ ደስታ ልቡን አያሞቀውም።

የሕሙማን ካርድ እያነበበ ልቡ ተራሮች እግር ስር የመሸጉ፣ የመሬት ሆድ ስር የተቀበሩ ዋሻዎችን ያስባሉ።

ሕክምና ተምሮ ቢያጠናቅቅም በልጅነቱ የነበረው ፍላጎት የዋሻ አሰሳ ፍቅር አልተወውም።

“በዚያን ጊዜ ስፒሊዮሎጂ ‘Speleology’ የሚለውን ቃል መጥራት ያስቸግረኝ ነበር። ስለዚህ ዘርፍ በኢንተርኔት ላይ ካየሁና ካወቅሁ በኋላ፣ ትምህርቱ የሚሰጠው የት ነው? የሚለውን መፈለግ ጀምርኩኝ። የዚህ ትምህርት ዘርፍ በአብዛኛው ጣልያን እና ፈረንሳይ አንደሚሰጥ አወቅሁ።”

ትምህርቱ ግን እንዲሁ አንደዋዛ ዘው የሚባልበት አይደለም።

በኪሱ የቋጠራትን ማውጣት ጠይቆታል። የገንዘብ፣ የጉዞ እና ሌሎች ውጣ ውረዶች ካሳለፈ በኋላ በጣልያን አገር በሚገኘው ክለብ አልፒኖ ኢታሊያኖ ‘Club Alpino Italiano’ በሚገኝ ተቋም በኢንተርኔት (ኦንላየን) ትምህርቱን ተከታተለ።

በመቀጠልም በዚሁ ዘርፍ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ፈረንሳይ በማቅናት የፈረንሳይ ስፒሊዮሎጂ ፌደሬሽን በሚባል ተቋም ለሁለት ዓመት ተምሮ ሙያውን ማጠናከር ቻለ።

በአሁኑ ጊዜም በኦሮሚያ የባህል እና ቴሪዝም ቢሮ ውስጥ በዚህ የሙያ ዘርፍ ተቀጥሮ እያገለገለ ሲሆን፣ ቢቢሲ ባነጋገረው ወቅትም ወደ ሶፍ ኡመር ዋሻ ሄዶ ነበር።

ናስር አህመድ የአገሪቱን ዋሻዎች ለመመራመር ከውጪ የሚመጡ ባለሙያዎችን ማገዝ፣ በጋራ በመሆን ጥናትንም ይሰራል።

ዋሻ በተራራ እና በመሬት ስር ብቻ ያለ ክፍት ቦታ ሳይሆን፣ ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት እና ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ነው።

“ቢሮ ተቀምጦ የሚሰራ ሥራ አይደለም”

ናስር ስለ ዋሻ እና ከዋሻ ጋር ተያያዥነት ስላላቸው ጉዳዮች ሲጠየቅ በትልቅ ፍቅር እና እውቀት ነው የሚያብራራው።

በሚሰራበት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ዋሻዎችን የእጁ መዳፍ ያህል ጠንቅቆ ያውቃቸዋል።

ሁሌም ልቡም እግሩም አዲስ ዋሻ ለማሰስ ስንዱ ናቸው።

በእርግጥ የስፒሊዮሎጂ ባለሙያ የሥራው ድርሻ በኦሮምያ ውስጥ ያሉ ዋሻዎች ቢሆኑም ወደ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ክልሎችም ተጉዞ ዋሻዎችን እንደ ጎበኘ እና አሰሳ ማካሄዱን ይናገራል።

“ኦሮሚያ ካሉት ዋሻዎች ውስጥ እስከ ዛሬ ያጠናኋቸው ወደ 321 የሚሆኑ ናቸው። ከእነዚያ ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት ካርታ እና ፕላን አላቸው። ይህንንም በመጽሐፍ አዘጋጅቻለሁ።”

ዋሻ በተራራ እና በመሬት ስር ብቻ ያለ ክፍት ቦታ ሳይሆን፣ ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት እና ብዙ ነገሮችን ያቀፈ ነው ይላል።

ከእነዚያ ውስጥም አብዛኛውን ጊዜ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች (ሮክ አርትስ) ሁልጊዜም እንደሚያስገርሙት ያነሳል።

በተለይ እርሱ እስካሁን በአሰሳቸው ዋሻዎች ውስጥ የተመለከታቸው ከ3000 – 7000 ዓመታትን ያስቆጠሩ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች የኦሮሞን ሕዝብ አኗኗር የሚያሳዩ አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ “ለቱሪዝም የሚሆኑ ማዕድናትን የያዙ፣ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ግብዓቶች ያሉባቸው፣ እንዲሁም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የዋሻ ዓይነቶች አሉ” ሲል ይገልጻቸዋል።

ናስር የዋሻ እና የዋሻ አካባቢን ምርምር እና አሰሳ ትዕግስት እና ትልቅ ጥንቃቄን እንደሚጠይቅም ይናገራል።

“ዋሻ፣ ቢሮ ውስጥ በመሆን የሚመረመር ነገር አይደለም። ብዙ ውጣ ውረድ አለው። ከከተማ ውጪ፣ በአመዛኙ ገጠራማ ቦታዎች ነው የሚገኘው። በእግር ለረዥም ሰዓት በመጓዝ ነው ወደ የዋሻዎች የሚደረሰው።

“እዚያ ተደርሶ ጥናት በሚጀመርበት ጊዜ ብዙ ነገር ያጋጥማል። እንደ እባብ፣ ዘንዶ እንዲሁም አንበሳ እና ነብርን ጨምሮ ልዩ ልዩ እንስሳቶች ዋሻዎቹን መኖርያቸው አድርገው ያጋጥማሉ።”

ይህ ባለሙያ እንደሚለው በዋሻዎቹ አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች፣ እዚያ ውስጥ ያለን የተፈጥሮ ሀብት ለማግኘት በሚል ለልዩ ልዩ አደጋዎች ሲጋለጡ አይቶ እንዳዘነም ይናገራል።

የሰዎችን አጽሞች ዋሻዎች ውስጥ አይቻለሁ። በዋሻዎች ውስጥ ያለው የአየር ሁኔታ “ከባድ” ነው የሚለው ናስር፣ ወደ ውስጥ ለመግባት እና ከተገባ በኋላም ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

“አንድ ዋሻ ለመግባት ከአለባበስ አንስቶ ጥንቃቄ ይደረጋል። ደኅንነቱ የተጠበቀ ጫማ እንዲሁም አራት አምስት መብራቶችን እንይዛለን። በተጨማሪም ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግል የሕክምና እርዳታ መስጫ ቁሳቁስ ይዘን እንገባለን።

“ጥልቀት ያለው ዋሻ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ዋሻ ውስጥ ወደታች የምንወርድበት ረዥም ገመድ እንጠቀማለን። ሌሎች ቁሳቁሶችን ደግሞ በጀርባችን ተሸክመን እንገባለን።”

ናስር ይህንን ሙያ በጣልያን እና ፈረንሳይ ተምሮ አጠናቅቋል።

ዋሻ በስሙ የተሰየመለት ናስር

ናስር አህመድ ለአስር ዓመት ያህል በዚህ የሙያ መስክ ላይ ቆይቶ፣ ዋሻዎችን ተመራምሮ የደረሰበትን ግኝት በመጽሐፍ መልክ ሰንዶ አሳትሟል።

“ከውጭ አገር ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ለአስር ዓመታት የሰነድኩትን ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ በማለት “ኬቭስ ኢን ኦሮሚያ” በሚል ርዕስ አሳትሜ አስመርቄያለሁ።”

መጽሐፉ ስለ ስፒሊዮሎጂ ምንነት፣ ዋሻዎች ውስጥ ለመግባት የሚደረጉ ጥንቃቄዎች፣ በኦሮሚያ የሚገኙ የዋሻዎች መገኛ ስፍራዎችን ይዟል።

የስፒሊዮሎጂ ባለሙያው ናስር አህመድ፣ ለዚህ ሙያው በተለያዩ ጊዜዎች እውቅናን አግኝቷል።

ነገር ግን ካገኛቸው እውቅናዎች ሁሉ እንደ ናሲኦል ዋሻ ልቡን በሐሴት የሚሞላው የለም።

“ኦሮሚያ ካሉ 321 ዋሻዎች ውስጥ ውበት ያለው እና በጣም ልዩ የሆነው ናሲኦል የሚባለው ዋሻ ሲሆን፣ በምሥራቅ ኦሮምያ መልካ በሎ ወረዳ ውስጥ ይገኛል።”

ናስር እንዴት ይህ ዋሻ በስሙ እንደተሰየመ ሲናገር በልዩ ደስታ ነው።

በዚያ ወረዳ ውስጥ አሁንም ያልታዩ (ያልተገኙ) ዋሻዎች አሉ የሚለው ናስር፣ የወረዳው ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ በአካባቢያቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያጠናላቸው ግብዣ ያቀርቡለት አንደነበር ጨምሮ ገልጿል።

“በወረዳችን ውስጥ አንድ ዋሻ የሚገኝ ከሆን በስምህ እንሰይማለን አሉኝ። እንደ ዕድል ሆኖ መግቢያው ከ30 – 60ሴሜ የሆነ እና በጣም ጠባብ የሆነ ዋሻ ጋራ ስር አገኘሁ። ሰውነቴ ለዋሻ የተፈጠረ ነው። ቢሆንም ግን እኔ እንኳ ከጠባብነቱ የተነሳ ሊያስገባኝ አልቻለም።”

ወደ ዚህ ዋሻ ውስጥ ለመግባት እስከ አምስት ሜትር የሚሆን መሬት ላይ ተኝቶ እየተሳበ መግባቱን የሚናገረው ናስር፣ ወደ ዋሻው ውስጥ ለመግባት የዋሻውን መግቢያ በመዶሻ እየሸራረፈ ማስፋቱን ይናገራል።

“እንደዚያ ሸራርፌ ያንን ዋሻ ሳገኘው ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። ስሜም ናስር ስለሆነ ይህ ዋሻ ናሲኦል መሆን አለበት ብዬ ሰየምኩት። እስከ ዛሬ ካገኘኋቸው ዋሻዎች ሁሉ ይበልጣል እንደማለት ነው። በኦሮሚያ ክልል ካሉ ዋሻዎች ሁሉ ያምራል። ክልሉም እውቅና ሰጥቶታል።”

ናስር ወደዚህ ሙያ ሲገባ በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል።

“ይህንን ሥራ በምጀመርበት ወቅት ሰዎች ለቤተሰቦቼ፣ ‘ልጃችሁ አብዷል ዋሻ ውስጥ ይዞራል’ ይሏቸው ነበር” በማለት አሁን ግን በሙያው ዙሪያ ያላቸው አስተሳሰብ እየተቀየረ እንደመጣ ይናገራል።

ናስር ቢሮ ውስጥ ከሚቀመጥበት ጊዜ ይልቅ በመስክ የሚያሳልፈው ይበልጣል።

አዳዲስ ዋሻዎችን ያስሳል፣ ይመዘግባል።

በቅርቡም በምሥራቅ ባሌ ዞን ዳዌ ቃጨን ወረዳ፣ ወደሚገኘው እና በዩኔስኮ ወደ ተመዘገበው የሶፍ ኡመር ዋሻ ይመላለሳል።

ለምን ካልን ደግሞ ሁለት ነገሮች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

አስገራሚ ነው ስለሚለው ስለዚህ ዋሻ በጥናት የደረሰበትን ወደ በመጽሐፍ የማዘጋጀት ሥራውን እያጠናቀቀ መሆኑን ተናግሯል።

በዚህ ውስጥም ከአሁን በፊት ታይተው የማይታወቁ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች፣ በግምት ከ2000 ዓመት በላይ የሚሆኑ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች ማግኘቱን እና በቅርቡም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

ናስር የታሪክ፣ የአርኪዮሎጂ እና የሌሎች ዘርፎች ባለሙያዎች ወደዚህ ዋሻ መጥተው ያሉትን ተያያዥ ጉዳዮች ማጥናት ቢችሉ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ማግኘት ይችላሉ ይላል።

በተጨማሪም መንግሥት የዚህን ዋሻ እና አካባቢውን ለማልማት የጀመረው ሥራ ጥሩ መሆኑን በማንሳት ይህም በባለሙያዎች መደገፍ እንዳለበት ይመክራል።