
ከ 8 ሰአት በፊት
ማርክ ዊሊያምስ ለ10 ዓመታት ያህል በቁማር ሱስ ሲሰቃይ ቆይቶ በስተመጨረሻ አቅሉን ሳተ።
በዕዳ ተዘፍቆ ሲባዝን ቆይቶ፤ የክሬዲት ካርዱ ዕዳ ተቆልሎ እንኳ 10 ሺህ ፓውንድ ሊመድብ ሲቃጣ ያየውን ማመን አቃተው።
ስክሪኑ “በቂ ገንዘብ የለህም” የሚል መልዕክት አሳየው።
የያዘውን አይፓድ ጨመቅ አደረገ። ቀጥሎ ከፊቱ ያለውን ሁሉ ከግድግዳ ጋር ያጋጨው ጀመር። የቤቱን ዕቃ በሙሉ ሰባብሮ ጨረሰ።
ጩኸቱን አቀለጠው። ስቅስቅ ብሎ ያቀለቅስ ያዘ። ራሱን ይረግም ገባ።
ዘወር ሲል የ18 ዓመቱ ጨቅላ ልጁ በአግራሞት ታየዋለች። “አፍጥጣ ታየኝ ነበር” ሲል ያስታውሳል። “ያንን ቀን መቼም አልረሳውም።”
“ራሴን አረጋጋሁ እና አንስቼ አቀፍኳት። ቀረብ አድርጌ እያየኋት ድምፄን ከፍ አድርጌ እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ ለራሴ ነገርኩት። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ የልጄ የወደፊት ዕጣ ላለማበላሸት ቃል ገባሁ።”
ይህ የሆነው በፈረንጆቹ ኅዳር 2018 ነው። ዊሊያምስ ከዚያች ‘የተረገመች ቀን’ በኋላ ቆምሮ አያውቁም።
ምንም እንኳ ዊሊያምስ ለልጁ ሕይወት ሲል ቁማር እርግፍ አድርጎ ቢተውም፣ የእግር ኳስ ሕይወቱን ግን ውሃ በላው።
አንድ ሰሞን እጅግ ተስፋ ያለው ሬክስሃም የተሰኘው ቡድን ተጫዋች የነበረው ይህ እግር ኳሰኛ፤ ጓደኞቹ ወደ እንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲያቀኑ እሱ ያገባሉ፤ አያገቡም እያለ ይቆምር ነበር።
የዌልስ ከ21 ዓመት በታች ቡድን እያለ አብረውት ኳስ ይጫወቱ የነበሩት እነ ሃል ሮብሰን-ካሉ እና ጆ አለን ዓለም በስክሪን ሲያያቸው እሱ ስክሪኑ ላይ ተደቅኖ ይመድባል።
“ሥልጠና ከሁሉ ቀድሜ የምገኝ፤ ከሁሉ ኋላ የምወጣ ነበርኩ። ነገር ግን ትንሽ ቆይቶ አርፍጄ መጥቼ ቀድሜ መውጣት ጀመርኩ።
“አሠልጣኞቹ የጠባይ ችግር ያለብኝ ይመስላቸው ነበር። ችግሩ ከዚያ የላቀ መሆኑን በፍፁም አልተረዱም።
“ሁለት ዓይነት ሕይወት ነበር የምመራው። ጠዋት ተነስቼ ጭምብል አጥልቄ እንደምወጣ ነበር የሚሰማኝ። ፊቴ ፈገግ ቢልም ልቤ ጨልሞ ነበር። የቡድን አጋሮቼን ፊት ማየት ተሳነኝ። ትክክለኛውን ማንነቴን የሚያዩቡኝ መለሰኝ።”
- የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታዎች ግምት – ማን ሊጉን ይሰናበታል?26 ግንቦት 2023
- ሜሰን ማውንት ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ማዲሰን ወደ አርሰናል?25 ግንቦት 2023
- “አንድ ሰሞን የክሪስቲያኖ እና ሜሲ የነበረው ላ ሊጋ. . .የዘረኞች ሆኗል”፡ የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪኒሲየስ ጁኒየር22 ግንቦት 2023
‘ፕሮፌሽናል’ አትሌቶች እና ቁማር
አንድ ወቅት የኤፍ ኤ ዋንጫ ጨዋታ ነበረበት። እናት እና አባቱ ጨዋታውን ሊታደሙ ከስታድየሙ ተገኝተዋል።
ዊሊያምን ያሳስበው የነበረው ግን በክሪኬት ጨዋታ የመደበው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ነው። ዳኛው ፊሽካ ነፍተው ወጥቶ ቁማር መብላት አለመብላቱን እስኪያውቅ ጓጉቷል።
“እግር ኳስ ተጫዋች መሆን ሰለችኝ። ከሁሉም ተነጥዬ ቁጭ ብዬ ቁማር መጫወት ሻትሁ።”
ድብቁ ሱስ ብለው የሚጠሩት የቁማር ሱስ እንደ አልኮሆል እና ሌሎች ሱሶች ሰውነታችን ላይ አሻራ አይተውም። ለዚህ ነው ብዙዎች ይህን ሱሳቸውን መደበቅ የሚሳካላቸው።
ሳይንቲፊክ ሪፖርትስ ጆርናል በዚህ ዓመት ባስጠናው ጥናት በአየርላንድ ‘ፕሮፌሽናል’ አትሌቶች ከሌላው ጊዜ እጥፍ የቁማር ሱስ እንዳለባቸው አጋልጧል።
ተቋሙ ከዚህ ቀደም በ2016 አውሮፓ ያሉ አትሌቶች በቁማር ሱስ እንደናወዙ በጥናቱ ገልጾ ነበር።
በ2014 የተሠራ ሌላ ጥናት ደግሞ ወንድ ‘ፕሮፌሽናል’ እግር ኳስ ተጫዋች እና የክሪኬት ተጫዋቾች ከሌለው የሕብረተሰብ ክፍል በበለጠ የቁማር ሱስ ተጠቂዎች መሆናቸውን ጠቁሟል።
በቂ የመዝኛ ጊዜ፣ ጥሩ ገቢ እና የማሸነፍ መንፈስ እነዚህ አትሌቶች በቁማር ሱስ እንዲጠቁ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሳይንሱ ይጠቁማል።
“አንዳንድ ያናገርናቸው ተጨዋቾች ሕይወታቸው ለቁማር የተሰጠ እንደሆነ ነግረውናል” ይላሉ አጥኚው ኪዬራን መሪ።
“በተፈጥሮ በጣም ተፎካካሪ ናቸው። ከቡድን አጋሮቻቸው ጋር ይቆምራሉ። ይህ ደግሞ ለቁማር ሱስ ያጋልጣቸዋል” ይላሉ።
ዊሊያምስ በዚህ ይስማማል።
“የቡድን አጋሬ ቁማር በልቶ እኔ ከተበላሁ የበለጠ እንድመድብ እሆናለሁ። ስሸነፍ ያንገበግበኛል። ሌሎችም ጓደኞቼ እንደዚህ ናቸው።”

አቋማሪ ድርጅቶች እና ማስታወቂያ
እንግሊዝ ውስጥ የእግር ኳስ ተጨዋቾች አማካይ ገቢ በሳምንት 60 ሺህ ፓውንድ ነው። ምንም እንኳ የሥልጠና የጨዋታ ጊዜያቸው እጅግ አድካሚ ቢሆንም በቂ የእረፍት ጊዜ አላቸው።
አልፎም አብዛኛዎቹ የሚልበሱት ማልያ በአቋማሪ ድርጅቶች አርማ ያሸበረቀ ነው።
ከዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች ስምንቱ የአቋማሪ ድርጅቶችን በማሊያቸው ከፊት ለፊት ያስተዋውቃሉ። ሁለት ቡድኖች ደግሞ እጀታቸው ላይ የድርጅቶች አርማ አለ።
የብሬንትፈርድ የማሊያ ስፖንሰር የደቡብ አፍሪካው አቋማሪ ኩባንያ ሆሊውድቤትስ ነው። ባለፈው ሳምንቱ የቡድኑ ዋና አጥቂ ኢቫን ቶኒ በቁማር ምክንያት ለስምንት ወራት ወደ እግር ኳስ ሜዳ ዝር እንዳይል ታግዷል።
ተጫዋቹ 232 የቁማር ሕግጋትን ጥሶ በመገኘቱ ነው ለዚህ ቅጣት የተዳረገው።
ምንም እንኳ ቶኒ የቁማር ሱስ አለበት ብሎ መናገር ባይቻልም የቡድኑ ዋና ስፖንሰር እና የተጨዋቹ በቁማር ምክንያት መቀጣት ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
ብዙዎች የእግር ኳስ አስተዳዳሪው ፌዴሬሽን ቡድኖች በአቋማሪ ድጅቶች ስፖርሰር እንዳይደረጉ ማገድ አለበት ሲሉ ይከራከራሉ።
አሁን አሁን ተጨዋቾች የቁማር ሱስ እንዳለባቸው በግልፅ መናገር ጀምረዋል።
የቀድሞው የአርሰናል ተጨዋቾች ፖል ሜርሰን በ2021 በሠራው ዘጋቢ ፊልም ከቁማር ሱስ እያገገሙ ያሉ ሦስት የቀድሞ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾችን አቅርቦ አናግሮ ነበር።
አራቱ ተጫዋቾች በቁማር ያጡትን ገንዘብ ሲያሰሉት ወደ 15 ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ ይደርሳል።
የቀድሞው የአርሰናል አምበል ቶኒ አዳምስ ‘ስፖርቲንግ ቻንስ’ የተሰኘ ክሊኒክ አቋቁሞ በቁማር እና በሌሎች ሱሶች የተጠመዱ የወቅቱ እና የቀድሞ ተጨዋቾችን ያግዛል።
በርካታ ሰዎች የሚስማሙበት አንድ ነገር አለ። የቁማር ሱስ እንደ አእምሮ ጤና መቃወስ ተደርጎ መቆጠር አለበት። አልፎም የተለያዩ የቁጥጥር መላዎች ይፋ እንዲደረጉ በመወትወት ላይ ናቸው።