May 27, 2023 – BBC Amharic 

ባለሥልጣኑ ያስመጠጠው የግድብ ዉሃ
የምስሉ መግለጫ,ባለሥልጣኑ ያስመጠጠው የግድብ ዉሃ

ከ 7 ሰአት በፊት

በሕንድ አንድ የአካባቢ ከፍተኛ ሹም ስልኬ ዉሃ ውስጥ ገብቷል በሚል ሙሉ ግድብ ውሃ አስመጠጠ።

ሹመኛው ስልኩ የግድብ ማቆርያ ውሃ ውስጥ የገባበት ምስለ ራስ ወይም ‘ሰልፊ’ በመነሳት ላይ ሳለ ነበር።

የባለሥልጣኑ ድርጊት በሕንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

ይህ ውድ የተባለው የዚህ ሹመኛ ስልክ ‘ሳምሰንግ’ ሲሆን በአሁኑ የገበያ ተመን 1ሺህ 200 ዶላር የሚያወጣ ነው።

ይህም በሕንድ ገንዘብ 100ሺህ ሩጲ ይተመናል።

የሹመኛው ስልክ በድንገት የሰመጠው በከርካታ ግድብ ነው።

ከርካታ ግድብ በማዕከላዊ ሕንድ ቻቲስጋር ግዛት ነው የሚገኘው።

ስልኩ በዚህ ግድብ ግዙፍ የውሃ ማቆርያ ውስጥ ከገባ በኋላ ጠላቂ ዋናተኞች ተጠርተው ስልኩን ከዉሃው ለማውጣት ብዙ የደከሙ ሲሆን ይህ ሳይሳካ ሲቀር ነው ሹመኛው ግድቡ በጠቅላላ እንዲመጠጥ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላለፈው።

የግድቡን ዉሃ በዲዚል መምጠጫ ለመምጠጥ ድፍን ሦስት ቀን ወስዷል ነው የተባለው።

በመጨረሻ ለግድብ የታቆረው ዉሃ ተመጦ ሲጠናቀቅ ስልኩ ቢገኝም ስልኩን ማስነሳት ግን አልተቻለም።

ይህ ሹመኛ ሚስተር ሺዋዛ ይባላል።

ለምን ለአንድ ስልክ ብሎ ሙሉ ግድብ ዉሃ እንዳስመጠጠ ሲጠየቅ ሳምሰንግ ስልኩ ቁልፍ መረጃዎችን ስለያዘ ነው ሲል ተከራርክሯል።

ይህ ሹመኛ የአካባቢው የምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው።

የግድቡን ዉሃ ለማስመጠጥ ከበላይ አለቃው የቃል ፍቃድ ማግኘቱንም ለሕንድ ሚዲያ ተናግሯል።

የሹመኛውን ስልክ ለማውጣት 2 ሚሊዯን ሊትር ዉሃ ወይም 440ሺህ ጋሎን ዉሃ ባክኗል።

ይህ የዉሃ መጠን 600 ሄክታር እርሻን ለማልማት በቂ ነበር።

ሹመኛው በዚህ ድርጊቱ እንደሚጠየቅና አሁን ከሥራ መታገዱን የሕንድ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

አንድ የዚህ ባለሥልጣን ማን አለብኝነት ያስቆጣቸው የሕንድ ፓለቲከኛ በትዊተር ገጻቸው፣ “በዚህ በጋ ሰዎች በውሃ ጥም እየተቃጠሉ፣ በታንከር ያቆዩትን ዉሃ በስስት በሚያዩበት በዚህ ወቅት ይህ የመንግሥት ባለሥልጣን 1ሺህ 500 ኤከር መሬት የሚያለማን ዉሃ ሲያባክን ዝም ተብሎ ይታያል?” ሲሉ ጽፈዋል።