
ከ 7 ሰአት በፊት
የሱዳን ተፋላሚዎች በጤና ማዕከላት እና በባለሙያዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ እንደ ጦር ወንጀሎች የሚቆጠሩ እንደሆነ መረጃዎች ጠቆሙ።
ህሙማን በጤና ማዕከላት ውስጥ ባሉበት ሁኔታ የአየር ጥቃትና በከባድ መሳሪያ ድብደባ የደረሰ ሲሆን ዶክተሮችም የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን ቢቢሲ አረብኛ ተመልክቷል።
ንጹሃን ላይ ሆን ብሎ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸም እንደ ጦር ወንጀሎች ሊታዩ እንደሚችሉም ተነግሯል።
በመዲናዋ ካርቱም ከሚገኙት 88 ሆስፒታሎች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጡም የሱዳን የዶክተሮች ህብረት አስታውቋል።
ቢቢሲ የሳተላይት መረጃዎችን፣ የካርታ ስራዎችን እንዲሁም ከተገልጋዮች የተገኙ ይዘቶችን በመፈተሽ እንዲሁም በርካታ የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገገር ሆስፒታሎች እና ክሊኒኮች ለሳምንታት በዘለቀው ጦርነት የደረሰባቸውን ጉዳት ፈትሿል።
የዓለም ጤና ድርጅት እነዚህን ጥቃቶች “የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ህግጋት በገሃድ የጣሰ ነው” ሲል ያወገዘ ሲሆን ጥቃቶቹም በአስቸኳይ እንዲቆሙም ተማጽኗል።
በሱዳን ጦር መሪ መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ መካከል ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7/ 2015 ዓ.ም ነበር።
የሚሊዮኖች ህይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።
የጤና ባለሙያዎች ህሙማንን እያከሙ በነበረበት ወቅት በአየር ጥቃት ወይም በከባድ መሳሪያ ኢላማ ከተደረጉ የጤና ማዕከላት መካከል በካርቱም የሚገኘው ኢብን ሲና ሆስፒታል አንዱ መሆኑን ቢቢሲ ተመልክቷል።
- ለአንድ ወር የዘለቀው የሱዳን ጦርነት16 ግንቦት 2023
- የሱዳኑ ጦር መሪ ምክትላቸውና ተፋላሚያቸውን ጄነራል ከስልጣን አሰናበቱ19 ግንቦት 2023
- በሱዳን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ያሉት ሁለቱ ጄነራሎች18 ሚያዚያ 2023
በሆስፒታሉ ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ሚያዝያ 11/ 2015 ዓ.ም ወቅት በስፍራው የነበሩት የቀዶ ጥገና ሃኪሙ ዶክተር አላ ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሱታል።
“ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ አልነበረም። እኔ የምሰራበት ኢብን ሲና ሆስፒታል በሶስት ቦምቦች ጥቃት ደረሰበት። አራተኛው ቦምብ የነርሶችን ቤት የመታ ሲሆን በዚህሙ ሙሉ በሙሉ ቤቱ ተቃጥሎ ወደመ” ብለዋል።
መንግሥታዊው ላልሆነ ድርጅት ‘ፊዚሻንስ ፎር ሂውማን ራይትስ’ ለተሰኘ ተቋም የዓለም ዓቀፍ የወንጀል ህግ ባለሙያ የሆኑት ክርስቲያ ደ ቮስ ጥቃቱ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠር እንደሚችል ተናግረዋል።
“የዓየር ጥቃቶች ከመፈጸሙ በፊት ንጹሃን ከሆስፒታሎች ለቀው መውጣታቸውን ማረጋገጥ በጦርነት ህጎች ውስጥ በግልጽ የተደነነገ ነው” ብለዋል።
የጥቃቱን ምስሎች የተመለከቱት የጦር መሳሪያዎች ባለሙያ ክሪስ ኮብ ስሚዝ በበኩላቸው በከባድ መሳሪያ ወይም በመድፍ የደረሱ ጥቃቶች ሊሆኑ እንደሚችሉም ተናግረዋል።
በነዚህ ጥቃቶች ላይ የዋለው የጦር መሳሪያ ላይ በትክክል ተለይቶ አለመታወቁ የትኛው ወገን ተጠያቂ እንደሆነ ወይም በነዚህ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ስለመሆኑ እርግጠኛ ለመሆን ፈታኝ አድርጎታል።