May 27, 2023 – BBC Amharic 

የፓወርቦል የሎተሪ ትኬት
የምስሉ መግለጫ,ከሳሽ ሎተሪው ተሰርቆብኝ ነው እንጂ የኔ ነበር ይላል

ከ 7 ሰአት በፊት

በአሜሪካ ባለፈው ኅዳር ወር 2 ቢሊዮን ዶላር የፓወርቦል ሎተሪ አሸናፊው የሆነው ግለሰብ ክስ ቀረበበት።

ዕድለኛው ኤድዊን ካስትሮ ላይ ክስ ያቀረበበት ግለሰብ ‘የአሸናፊ ትኬቱ የኤድዊን ካስትሮ ሳይሆን የኔ ነው’ ይላል።

የ2 ቢሊዮን ዶላር አሸናፊው ኤድዊን ካስትሮ ነዋሪነቱ በካሊፎርኒያ ግዛት ነው።

ከሳሽ ጆሴ ሪቬራም እንዲሁ የካሊፎርኒያ ነዋሪ ሲሆን ለፍርድ ቤት ባቀረበው የፍትሐ ብሔር ክስ 2 ቢሊዮን ዶላሩ የሚገባው ለኔ ነው ብሏል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ዕድለኛ ኤድዊን ካስትሮ ያለው ነገር የለም።

ከሳሽ ጆሴ ሪቬራም ለምን የአሸናፊ ቁጥሩ የኔ ነው እንዳለ ማስረጃዎቹ ገና ይፋ አልሆኑም።

ሆኖም የካሊፎርኒያ ፓውርቦል ሎተሪ አስተዳደር ከዚህ ቀደም አሸናፊው ኤድዊን ካስትሮ ለመሆኑ መቶ በመቶ እርግጠኞች ሆነናል ብሎ ነበር።

በየካቲት ወር ሎተሪ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ ‘ሁልጊዜም ቢሆን አሸናፊዎቹ በእርግጥም ትክክለኛ አሸናፊ ናቸው ወይ የሚለውን በጥንቃቄ እንመረምራለን።’ ብሎ ነበር።

ሪቨራ የፍትሐ ብሔር ክስ ያቀረበው በአልሀምብራ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው።

ከሳሽ እንደሚለው ከሆነ ትኬቱን በኅዳር 7፣ 2022 እንደገዛውና በዚያው ዕለት ላይ በአንድ ግለሰብ መሰረቁን ተናግሯል።

ቴኬቱን የሰረቀው ግን አሁን ዕድለኛ የሆነው ኤድዊን ካስትሮ እንዳልሆነ አብራርቷል።

ይሁንና ትኬቱ እንዴት በኤድዊን ካስትሮ እጅ ሊወድቅ እንደቻለ የተባለ ነገር የለም።

የፓውርቦል የ2ቢሊዮን ዶላር ሎተሪ አሸናፊዎች ማሸነፋቸው ከተረጋገጠ በኋላ ሁለት አማራጮች ይቀርብላቸዋል።

አንዱ አማራጭ ገንዘቡን በአንድ ጊዜ አፍሶ መውሰድ ሲሆን ሁለተኛው አማራጭ ግን ለሚቀጥሉት 29 ዓመታት ገንዘቡ ተቆራርጦ የመውሰድ አማራጭ ነው።

አሸናፊዎቹ የመጀመርያውን አማራጭ ከመረጡ፣ ማለትም በአንድ ጊዜ ይሰጠኝ ካሉ ወደኪሳቸው የሚገባው ገንዘብ 2ቢሊዮን ዶላር ሳይሆን 997.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

ነገር ግን በ29 ዓመታት ተከፋፍሎ ይሰጠን ካሉ ከሞላ ጎደል 2 ቢሊዮን ዶላሩ የነርሱ ይሆናል።

ብዙውን ጊዜ ታዲያ ሁሉም አሸናፊዎች ማለት ይቻላል የሚወስዱት አማራጭ የመጀመርያውን ነው።

በአሜሪካ ፓውርቦል ሎተሪ ከ50 ግዛቶች ውስጥ በ45ቱ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በዋሺንግተን ዲሲ እና የአሜሪካ አካል የሆኑት ደሴቶቹ ፖርቶሪኮ እና ቨርጂን አይላንድም በሎቶሪው ጨዋታ ይካተታሉ።

በአሜሪካ ሎተሪ አሸናፊዎች ጠጠር ያለ የፌዴራል ግብር መክፈል ይኖርባቸዋል። ይህም ከ24 እስከ 37 በመቶ ይሆናል።

አሸናፊዎቹ ከፌዴራል ግብር ሌላ የግዛት ግብርም ሊኖርባቸው ይችላል። ሆኖም ከ45ቱ ሎተሪው ከሚገኝባቸው ግዛቶች ዐሥሩ የግዛት ግብር በሎተሪ ላይ አያስከፍሉም።

አሸናፊው ካስትሮና ከሳሹ የሚገኙባት ካሊፎርኒያ አጋጣሚ ሆኖ ሎተሪ አሸናፊዎችን ግብር ከማይጠይቁት ዐሥር ግዛቶች አንዷ ናት።

አሸናፊዎቹ ለምሳሌ የኒውዮርክ ግዛት ነዋሪ ከሆኑ ደግሞ ከፌዴራልና ከግዛት ግብር በተጨማሪ የማዘጋጃ ግብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ።