
ከ 6 ሰአት በፊት
በአሜሪካዋ ኮነቲኬት ግዛት ከ370 ዓመታት በፊት በጥንቆላ ተግባር ጥፋተኛ ተብለው የነበሩ ግለሰቦች ከጥፋታቸው ነጻ እንዲባሉ ምክር ቤቱ ወሰነ።
ከምዕተ ዓመታት በኋላ ነጻ እንዲሆኑ የተበየነላቸው 12 ግለሰቦች አሜሪካ በቅኝ ግዛት በያዘቻቸው ስፍራዎች ነዋሪዎች ነበሩ።
ከ12ቱ አስራ አንዱ ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ በስቅላት እንዲቀጡም ተበይኖባቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የግዛቲቷ ምክር ቤት ያንን የፍርድ ሂደትም በመመርመር “የፍትህ ጉድለት” የታየበት ነው ብሏል።
በስህተት ጠንቋይ ናቸው ተብለው የተከከሱትን ሰዎች ስም ለማጥራት የልጅ ልጆቻቸው ለዘመናት የዘለቀ እልህ አስጨራሽ ዘመቻና ትግል አካሂደዋል።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካ በርካቶች ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ አሰቃቂ ግድያዎች ተፈጽሞባቸዋል።
በያዝነው ሃሙስ የኮነቲኬት ምክር ቤት በ1600 አጋማሽ እስከ መጨረሻው ድረስ በግዛቲቷ ውስጥ በጥንቆላ የተከሰሱትን ለማውጣት 33 ለአንድ በሆነ ብልጫ ድምጽ ሰጥቷል።
ይህንን ውሳኔ በመቃወም ድምጽ የሰጡት ሴናተር ሮብ ሳምፕሰን የተባሉት የምክር ቤት ተወካይ ናቸው።
“እኛ ልንረዳቸው የማንችላቸውን ያለፉት ጊዜያት ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች ትክክል ወይም ስህተት ነው ብሎ መመርመሩ ስህተት ነው” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል ።
“አሜሪካ እንደ መጥፎ የታሪክ ቦታነት ለመሳል የሚሞክሩ ሁነቶችን ማየት አልፈልግም” ሲሉ መናገራቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
“የወደፊቱ ላይ እንድናተኩር እፈልጋለሁ። ይህ የበለጠ ብሩህ እና የተሻለ ነው” ብለዋል።
የውሳኔ ሃሳቡ ቀደም ሲል በኮነቲኬት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ121 የድጋፍ ድምጽ እና በ30 ተቃውሞ አልፏል።
- በስሙ ዋሻ የተሰየመለት ኢትዮጵያዊው የዋሻዎች ተመራማሪከ 9 ሰአት በፊት
- በሱዳን ሆስፒታሎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመከ 7 ሰአት በፊት
- ሞባይል ስልኩ ዉሃ ውስጥ የሰመጠበት ሹመኛ ሙሉ የግድብ ዉሃ እንዲመጠጥ አስደረገከ 8 ሰአት በፊት
በጥንቆላ ተወንጅለው በነበሩ የልጅ ልጆችና ዘመዶች የተመሰረተው “ጠንቋዮችን ነጻ የማውጣት ፕሮጀክት” ከአውሮፓውያኑ 2005 ጀምሮም ስማቸውን ከጥፋት ነጻ ለማድረግ ሲሟገት ቆይቷል።
ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል የዘለቀውንም ዘመቻ ተከትሎ ነው ይህ ብያኔ የተላለፈው።
ቡድኑ በዚህ ውሳኔ ከፍተኛ ደስታም እንደተሰማቸውና ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ብያኔው የመጀመሪያ ጠንቋይ ተብላ በኒው ኢንግላንድ ተፈርጃ የተሰቀለችው አሊስ ያንግ 376ኛ ዓመት ዋዜማም ላይ መሆኑም ደስታቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ነው።
“ለዚህ ብያኔ አስተዋጽኦ ላደረጉ የልጅ ልጆች፣ ተሟጋቾች፣ ዘመዶች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሁለቱም ፓርቲዎች ህግ አውጭዎችና ሌሎችንም እናመሰግናለን” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በታሪክ ትምህርትም እና በተለያዩ ሁኔታዎች በጥንቆላ ችሎት ሰለባ የሆኑትን ለማስታወስ ጥረት ማድረጋቸውንም እንደሚቀጥሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጥንቆላ ተወንጅለው የተገደሉ ግለሰቦች የልጅ ልጆችና ዘመዶች ግለሰቦቹን ከዚህ ጥፋት ነጻ ማድረግ ከታሪክ ጥፋት ለመማር አስፈላጊ እርምጃ ነው በማለትም ይከራከራሉ።