
ከ 6 ሰአት በፊት
በአሜሪካ ሚሲሲፒ ግዛት ፖሊስ ‘ትልቅ ሰው መስሎኝ ነው የተኮስኩበት’ ያለው የ11 ዓመት አዳጊ የፍትሕ ያለህ እያለ ነው።
አዳጊው ጥያቄውን ያቀረበው በጠበቃው በኩል ነው።
ጠበቃ ካርሎስ ሙር ‘በፍጹም ይህ ትንሽ ልጅ ትልቅ ሰው አይመስልም፤ ፖሊስ ‘ትልቅ ሰው መስሎኝ ነው የተኮስኩበት’ የሚለው ነገር ብዙም ስሜት አይሰጥም፤ በልጁ ስም ፍትሕ እንጠይቃለን ብለዋል።
ይህ አዳጊ ስሙ አድሪየን ሙሪ ይባላል።
ባለፈው ቅዳሜ ነበር ቤት ውስጥ እናቱና የእንጀራ አባቱ አለመግባባት ውስጥ ስለነበሩ ‘911’ ደውሎ ፖሊስ የጠራው።
ፖሊስ ገና ከመድረሱ በቤታቸው ፊት በር ሆኖ ይህን ቤት ውስጥ የነበረውን ልጅ ነጥሎ ደረቱ ላይ ይተኩስበታል።
የአዳጊው እናት ናካላ ሙሪ እንደተናገረችው ልጇ ደረቱ ላይ ከተተኮስበት በኋላ ራሱ “ለምንድነው የተተኮሰብኝ?” እያለ ያለቅስ ነበር።
በአዳጊው ደረት ላይ ጥይት አነጣጥሮ የተኮሰው ፖሊስ ለጊዜው የግዳጅ እረፍት ወስዷል።
አዳጊ አድሪያን ሙሪ ሕይወቱ የተረፈች ሲሆን አሁን ከነበረበት ሆስፒታል ወደ ቤት ተመልሶ እያገገመ ነው።
ሙሪ ሳንባው እና ጎድኑ አካባቢ እንዲሁም ጉበቱ በመጎዳቱ በሆስፒታል ሕክምና ተደርጎለታል።
ባለፈው ቅዳሜ ማለዳ ፖሊስ ከነ ሙሪ ቤት ጥሪ ከደረሰው በኋላ ስፍራው ደርሶ “ቤት ውስጥ ያላችሁ በሙሉ እጃችሁን ወደ ላይ እያደረጋችሁ ወደ ደጅ ዉጡ” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ይሰጣል።
ይህ ልጅ ታዲያ በቤቱ ኮሪደር ላይ ወዲያ ወዲህ እያለ ነበር በዚህ ወቅት።
ፖሊስ ከደጅ አነጣጥሮ ደረቱን የመታውም በዚሁ ጊዜ ነው።
ልጁ መሬት ላይ ከተዘረረ በኋላ አምቡላንስ እስኪደርስ እናቱ እና ተኩሶ የመታው ፖሊስ የመጀመርያ እርዳታ አደርገውለታል።
- በጦር መሣሪያ ፍቅር የወደቀችው አሜሪካ4 ጥቅምት 2017
- በአሜሪካ ቴክሳስ ታጣቂው የ8 ዓመት ሕጻንን ጨምሮ 5 ጎረቤቶቹን ተኩሶ ገደለ30 ሚያዚያ 2023
- ሎተሪ በአንድ ጀንበር ሚሊዬነር ያደረጋቸው ሰዎች ምን አሉ?30 ጥር 2021
ጠበቃው እንደሚለው አዳጊ አድሪየን ሙሪ ቁመቱ 1 ሜትር ከ47 የሆነ ልጅ ነው፤ በፍጹም አዋቂ ነው ብሎ ለመሳሳት አይመችም፤ ፖሊስ ድርጊቱን ተሳስቶ አልፈጸመም ይላል።
ፖሊስ ተሳስቶ እንኳ ቢሆን አዳጊ ሙሪ በእጁ ምንም ዓይነት መሣሪያም ሆነ ሌላ አሳሳች ነገር አልያዘም፤ ‘ፖሊስ ለምን ተኮሰ ታዲያ?’ ሲልም ይጠይቃል።
አዳጊው ሙሪ ያን ጠዋት ፖሊስ ዘንድ እንዲደውል ያዘዘችው እናቱ ስትሆን የሌሎቹ ልጆቿ አባት ባህሪ ስላላማራት ነበር ሙሪን በአፋጣኝ ፖሊስ ደውሎ እንዲጠራ ያዘዘችው።
ጠበቃው እንደተናገረው “ይህ ልጅ አሁንም ድረስ ለምን ፖሊስ ተኩሶ ደረቱን እንደመታው ሊገባው አልቻለም፤ በየቀኑ ይጠይቀናል፤ ይህን ጥያቄ የሚመልስለት ማን ነው?”
የኢንዲያኖላ አካባቢ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ለጊዜው በክስተቱ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
የከተማዋ ከንቲባ ኬን ፊዘርስቶን ግን ለአካባቢው ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፣ ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊስ ለጊዜው በግዳጅ እረፍት ላይ ሆኖ የሥነ ልቡናና ተያያዥ ምርመራ እየተደረገለት ነው ብለዋል።
ይህን ድርጊት ቀርጾ የያዘ ካሜራ የሚገኝ ሲሆን ፖሊስ ግን ለጊዜው ለሕዝብ ዕይታ አላበቃውም። ተንቀሳቃሽ ምሥሉ በመርማሪዎች እጅ ነው የሚገኘው።
የአዳጊው ጠበቃ ግን ተንቀሳቃሽ ምሥሉ ይለቀቅ፤ ሕዝብም ይፍረደን እያሉ ነው።