May 27, 2023 – Konjit Sitotaw

ይህ እየተካሄደ ያለው የትዊትር ዘመቻ፤ በመጪዎቹ ሳምንታትና ወራት በሰላማዊና ህዝባዊ እምቢተንኝነት የትግል ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ተጨማሪ የትግል ዘርፎችን ይዞ የሚመጣ ይሆናል። እነዚህ የትግል ዘርፎች ተጨባጭ ህዝባዊ እምቢተኝነትንና ከዚህ ፍጹም ጨቋኝና ኢፍትሃዊ ከሆነው በኢትዮጵያ ካለው አገዛዝ ጋር ያለመተባበር ጥሪን ይጨምራል።

ይህ ዘመቻ የእንቅስቃሴያችን ጅማሮ ብቻ እንጂ ዋናው የትግሉ መዳረሻ ጉልላቶች ይሚከተሉት ናቸው፤


o የአብይ አህመድ መንግስት በአግባቡ ተጠያቂ ማድረግ፤
o በኢትዮጵያ መረን ያጣውን የጭቆናና የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም፤​
o በ10ሸዎች በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብአዊ የሆነ የቤት ፈረሳና ማፈናቀልን ምግታት፤
o በአማራዎች፣ በጋዜጠኞችና በማህበራዊ አንቂዎች ላይ በስፋት እየተካሄደ የሚገኘውን ማንነትን ያማከለ እገታና ህገወጥ አፈሳና እስርን ማስቆም፤
ዘመቻው ክዚህም በተጨማሪ በአገዛዙ በከፍተኛ ባለስልጣኖችና ሸሪኮቻቸው ጥምረት እየተፈጸሙ ያሉ ግዙፍ፣ ሀገርን የሚያቆረቁዙ ዘረፋዎችንና የሙስና ወንጀሎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ የማድረግ ዓላማ አንግቧል። በወለጋ በበርካታ ዙር በአማራዎች ላይ የተካሄደውን ማንነት ተኮር ጭፍጨፋና ማባሪያ ያጣውን ማፈናቀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ማድረግ፣ በአዲስ አበባና አካባቢው የተንሰራፋውን እና ስርአታዊ እየሆነ የመጣውን የማግለል፣ አድሎና የዜጎች መጎሳቆል ባግባቡ ማጣራትና መቋጫ መስጠት በዘመቻው እንደግብ ከተቀመጡት መሃከል ይገኙበታል።

ከዚህም ባለፈ በተለየ መልኩ ላለፉት 30 ዓመታት በጠላትነት ተፈርጆ፣ በሀገሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ይህ ነው የሚባል ተሳትፎና ሚና እንዳይኖረው በማግለል፣ በግላጭ የጥላቻና የጎሳ ፖለቲካ ሀ ሁ ማለማመጃ ተደርጎ ተዘርዝሮ ለማያልቅ ግፍ እና መከራ ሲዳረግ ለከረመው ሰፊው የአማራ ህዝብ፣ ከአምስት አመት ወዲህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርበት ለውጥና ስርዓት ሊመጣ ነው ሲባል ከወንድምና እህት ኢትዮጵያዊያን ጋር ብዙ መስዋዕት የከፈለ፣ ብዙ መከራን የተቀበለው ይህ ማህበረሰብ በተመሳሳይ ባለፉት 5 ዓመታት ዘግናኝ ጭፍጨፋና ማፈናቅል እያስተናገደ ቀጥሏል። በነዚህ እረጅም የመከራ አመታት ፍትህ የናፈቀው፣ እንደሰው ተቆጥሮ የተፈጥሮ በህይዎት የመኖር መብት እንደሰማይ የራቀው የአማራ ህዝብ፤ አሁን ዛሬ ደግሞ አዲስ ክህደት፣ ጭፍጨፋ፣ ማፈናቅል፣ ጅምላ እስር፤ ታውጆበት ፍዳውን እያየ ይገኛል። ይህ የአማራ ህዝብ በቅርቡ በተደረገው የሰሜኑ ጦርነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቁመናው የደቀቀና በሚሊዮኖች ተፈናቃዮች የተሞላ አካባቢ መሆኑ ደግሞ ጉዳቱን ተደራራቢ ያደርገዋል። ይህ ሁሉ በዓለም ለሰው ልጆች የሚታወቁ መከራዎች መሸከሙ አልበቃ ብሎ የኦሮሚያው ብልጽኛ ፣ያለአንዳች አሳማኝ ምክንያትና ህጋዊ መሠረት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በአማራ ክልል ላይ በማዝመት በዚህ የእርሻ ወቅት ገበሬውን፣ ውጣቱንና መላውን የአማራ ማህበረሰብ እያሸበረ ይገኛል። የግፍም ልክ አለው! የመከራም ማብቂያ አለው! የክህደትም ጣራ አለው! ይህ በፍጹም ተቀባይነት የለውም። ይህ ግፍ በአስቸኳይ ካልቆመ ለአማራውና የኦሮሚያ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን መላውን ኢትዮጵያ በጅምላ ወደማንወጣበት መቀመቅ የሚወስድ ይሆናል።
በተያያዘ፤ ዘመቻው በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውን ህገ ውጥና ምንም አይነት ህገመንግስታዊ መሠርት የሌላቸውን መመሪያዎችን የማጋለጥና የማስዎገድ ዓላማ አለው።

የኦሮሚያ ብልጽግና ተብዬው በጠራራ ጸሐይ በሀገርና የህዝብ ሀብት ላይ እየፈጸመ ያለውን መዋቅራዊና ስራዓታዊ ዘረፋ፣ ወደ አጎራባች ክልሎች የሚጭረውን ተደጋጋሚ ትንኮሳና የመሬት ወረራ በአስቸኳይ ማቆም ይግባዋል እንላለን። ከዚህም አልፎ በአጠቃላይ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ባህል፣ ፖለቲካና ተቋማት በደባ፣ ያለይሉኝታ በመቆጣጠር በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የባርነት ቀንበርን ለመጫን የሚደረግ መፍጨርጨር፤ ከቅርቡ ከወያኔ የቀቢጸተስፋ ታሪክ እንኳ ትምህርት መውሰድ አለመቻሉ የሚያስቆጭ ድንቁርና እንደሆነ ብንገነዘብም፣ በዝምታ የምንቀበለው ሳይሆን አምርረን የምንታገለው ይሆናል።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አንገብጋቢ ሀገራዊ ህጸጾችን ከማከም ይልቅ ጌጡ ያደረገና፣ ለወንጀሎቹ ተጠያቂነትና ማስተካከያ ሳያበጁ፤ ይህ ህዝባዊና ፍትሃዊ ዘመቻ ከቶ እንዴት ይካሄዳል ብሎ ለመሞገት የሚያበቃ የሞራል ልዕልና ከወዴት ሊመጣ ይችላል?

ባጭር ታጥቀን የገባንበት ህዝባዊና ፍትሃዊ ዘመቻ የሚከተሉት ወሳኝ ማሳሰቢያዎች/ ጥሪዎችን አስቀምጧል፤
ሀ/ ለኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ አባላት፤ #DoNotFeedTheBeast ላብህን አንጠፍጥፈህ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በባንክና መንግስታዊ በሆኑ የገንዘብ ማስተላለፊያዎች በመላክ ወገንዎን በማስጨነቀ የተጠመደውን የጨካኙን አገዛዝ ጡንቻ አያፈርጥሙ። (ከመንግስት ውጭ በሆኑ አማራጭ የገንዘብ ማስተላልፊያ መንገዶች ይጠቀሙ)።
ለ/ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚደረግ ማናቸውም የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ድጋፍ መንግስት በተጨባጭ ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ በሚያሳየው ቁርጠኝነት፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለበት የመንግስት አስተዳደር ምርሆ ላይ ባለው ስርዓትና አፍጽጸም አግባብ እንዲሆን ማስቻል። ከዚህ በተቃራኒው የኢትዮጵያ አጋሮችና ሀገራት፤ ዕለት ከዕለት በጭካኔና በፍጹም ኢፍትሀዊነት ባቡር ላይ ተቀምጦ ሀገሪቱን ወደለየለት በዘርና በቋንቋ ወደተዋቀረ አሀዳዊና አምባገነናዊ ስርዓት እያንደራደራት ለሚገኝ ቡድን የሚያደርጉትን መርህ አልባ እርዳታና ድጋፍ ባስቸኳይ ሊያቆሙ ይግባል።