
ከ 5 ሰአት በፊት
ዩክሬን ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የሃገሪቱ ከፍተኛ የደህንት ባለስልጣን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ኦሌክሲይ ዳኒሎቭ አገራቸው በሩሲያ ላይ ልታደርገው ያቀደችውን መልሶ የማጥቃት ዘመቻ መቼ እንደሚጀመር ቀኑን በትክክል አልገለጹም።
ነገር ግን ዩክሬን በወረራ የተወሰደባትን ግዛቶች ለማስመለስ የሚደረገው ጥቃት “ነገ፣ ከነገ ወዲያ ወይም ከሳምንት” በኋላ ሊጀምር ይችላል ብለዋል።
የዩክሬን መንግሥት በዚህ ውሳኔ ላይ ስህተት የመፈጸም ቦታ የለውም ሲሉ አስጠንቅቀውም “ልናጣው የማንችለው ታሪካዊ አጋጣሚ” ነው ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ጸሃፊ የሆኑት ኦሌክሲይ ዳኒሎቭ የፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የጦርነት ካቢኔ ቁልፍ ሰው ናቸው።
ኦሌክሲይ ከቢቢሲ ጋር እያደረጉት የነበረው ያልተለመደ ቃለ ምልልስም ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በመልሶ ማጥቃቱ ላይ ለመወያየት ስብሰባ እንደጠሯቸውም በደረሳቸው የስልልክ መልዕክት ተቋርጦ ነበር።
ኦሌክሲይ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ዋግነር ወታደሮች ከባኸሙት ከተማ ለቀው እየወጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
- የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) በሱዳን ምን እየሠራ ነው?25 ሚያዚያ 2023
- ዩክሬን ለወራት ስትዘጋጅ እና ስትታጠቅበት የቆየችው መልሶ ማጥቃት ምን ሊቀይር ይችላል?16 ግንቦት 2023
- የሩሲያን ድንበር ደፍረው በመሻገር ፑቲንን እየተዋጉ ያሉት ሚሊሻዎች ማን ናቸው?24 ግንቦት 2023
የባኽሙት ከተማ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደባቸው ስፍራዎች አንዷ ናት።
“ወደ ሌሎች ሶስት ቦታዎች እየተሰባሰቡ ነው ሆኖም ውጊያ ያቆማሉ ማለት ግን አይደለም” ብለዋል ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣኑ
ኦሌክሲይ በተጨማሪም ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ወደ ቤላሩስ አሰርማታለች መባሉ ምንም እንደማያስፈራቸውም ተናግረዋል። “ይህ ለእኛ አዲስ ዜና አይደለም” ብለዋል።
ዩክሬን በሩሲያ ላይ መልሶ የማጥቃት ዘመቻን ለመክፈት ለወራት ያህል ስታቅድ ነበር። ወታደሮችን ለማሰልጠን እና ከምዕራባውያን አጋሮቿም የጦር መሳሪያዎችንም ለማግኘትም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ሊደርስ ይችላል የተባለውን መልሶ የማጥቃት ዘመቻም ለመከላከል ዝግጅቷን አጠናክራለች ተብሏል።
የዩክሬን መንግሥት ለህዝቡም ሆነ ለምዕራባውያን አጋሮቹ የሩስያን ኃይል ጥሶ ሉዓላዊ ግዛቶቹን ማስመለስና እንዲሁም ይህ ወታደራዊ ውዝግቡም እንዲያከትምም እንዲያሳይ እየተጠበቀ ይገኛል።