በተከዜ አዋሳኝ የሚገኙ የጠለምት ነዋሪዎች በህወሓት ታጣቂዎች ትንኮሳ እየተፈፀመብን ነው አሉ
ነዋሪዎቹ በሚደርስባቸው ትንኮሳ ከአካባቢያቸው እየተፈናቀሉ መሆኑን ገልጸዋል
(አዲስ ማለዳ) በተከዜ አዋሳኝ የሚገኙ የጠለምት አካባቢ ነዋሪዎች የህወሓት ታጣቂዎች ልምምድ እያደረጉ እና ትንኮሳ እየፈጸሙብን ነው ሲሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዚህም ትጥቅ ያልፈቱ የህወሓት ኃይሎች በጠለምት ሦስት ቀበሌዎችን በመቆጣጠራቸው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተናግረዋል፡፡
በምስራቅ ጠለምት ወረዳ ሥር የሚገኙት ሜዳ፣ ምድረ አምሾ፣ እና ደገብራይ የሚባሉ ሦስት ቀበሌዎች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ሕብረተሰቡ ለከፋ ችግር ተጋልጧል ነው የተባለው።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ትጥቅ ያልፈቱት የህወሓት ታጣቂዎች መድፍን ጨምሮ ሞርታር፣ ዙ-23 እና ሌሎች ከባድ መሳሪዎችን ይዘው እንደሚንቀሳቀሱም ተገልጿል፡፡
ታጣቂዎቹ በአካባቢው የጦር ልምምድ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ የተባለ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ በሚደርስባቸው ትንኮሳ እየተፈናቀሉ መሆናቸው ተመላክቷል።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች መሳሪያ ማስረከብ የሚኖርባቸው ቢሆንም፤ ሙሉ በሙሉ አለማስረከባቸው እና በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ትንኮሳ እንደሚፈጽሙ ይገለጻል፡፡
በሌላ በኩል፤ በትናንትናው ዕለት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች መቀለ አቅራቢያ በሚገኘው ላጪ ተብሎ በሚጠራው ቦታ፣ የቡድን መሳሪያዎችን ለመከላከያ ሠራዊት ተወካዮች ማስረከባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ርክክቡ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ማረጋገጥ ኮሚቴ አባላት በተገኙበት መከናወኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በርክክቡም የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች በእጃቸው የነበረ የቡድን መሳሪያ ማለትም ዲሽቃ፣ አርፒጂ፣ መትረየስና ሞርታር የተባሉ የጦር መሳርያዎችን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማስረከባቸው ተነግሯል።