
28 ግንቦት 2023, 10:22 EAT
ቻይና በአገሯ ውስጥ ያመረተችው የመጀመሪያው የመንገደኞች ጄት አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን ይዞ የተሳካ የመጀመሪያውን የንግድ በረራ አደረገ።
የአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ሲ919 የተባለው አውሮፕላን ተሳፋሪዎችን ይዞ ዛሬ እሁድ ጠዋት ከሻንግሃይ በመነሳት ወደ ዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ሲያመራ አሳይቷል።
ይህ የቻይና የመጀመሪያው የመንገደኞች አውሮፕላን ኮሜርሺያል አቪዬሽን ኮርፖሬሽን ኦፍ ቻይና (ኮማክ) በተባለው ድርጅት የተሰራ ሲሆን፣ በኤርባስ እና በቦይንግ ጄቶች በበላይነት የተያዘውን የአውሮፕላን ምርት ዘርፍ ሰብሮ ለመግባት አገሪቱ ያያዘችው ዕቅድ ነው።
ነገር ግን ይህ 164 መቀመጫዎች ያሉት በቻይና የተሰራው አውሮፕላን ሞተሩን ጨምሮ አብዛኛውን ወሳኝ ክፍሎቹን የሚያገኘው በምዕራብ አገራት ውስጥ ከሚገኙ የአየር በረራ ቴክኖሎጂ አምራቾች ነው።
- ዶናት ጋጋሪው፣ የሎሚ ጭማቂ አዟሪው፣ ሰሊጥ ቸርቻሪው ጣይብ ኤርዶዋን ማን ናቸው?28 ግንቦት 2023
- በአሜሪካ ገንዘብ ተቀብሎ አስከሬኖችን ለወራት ያስቀመጠው ቀብር አስፈጻሚ በፖሊስ ተያዘ28 ግንቦት 2023
- ፒኤስጂ በሊዮኔል ሜሲ ግብ ታግዞ የፈረንሳይ የሊግ 1 ዋንጫን አነሳ28 ግንቦት 2023
የመጀመሪያው አውሮፕላን ከ130 በላይ መንገደኞችን በማሳፈር ከሻንግሃይ ወደ ቤይጂንግ ያደረገውን ቀዳሚ የንግድ በረራውን ከሦስት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ችሏል።
አውሮፕላኑ በተጨማሪም ከቤይጂንግ ወደ ተነሳባት የባሕር ዳርቻ ከተማዋ ሻንግሃይ የመልስ ጉዞ እንደሚያደርግም ፕሮግራም ተይዞለታል።
የቻይና መንግሥት ንብረት የሆነው ቻይና ኢስተርን አየር መንገድ፣ አምስት ተመሳሳይ አውሮፕላኖች እንዲመረቱለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አውሮፕላኑን ያመረተው ኮማክ የተባለው ተቋም በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ 150 አውሮፕላኖችን ለማምረት ዕቅድ ይዟል።
ጨምሮ እንደገለጸውም አስካሁን 1,200 ሲ919 የተባሉትን የመንገደኞች አውሮፕላኖችን እንዲያመርት ከተለያዩ አየር መንገዶች ትዕዛዝ ተቀብሏል።
አንዳንድ የአየር ትራንስፖርት ባለሙያዎች እንዳሉት ግን ይህ ከተጠቀሱት የአውሮፕላን ምርት ትዕዛዞች ውስጥ አብዛኞቹ ከአገር ውስጥ አየር መንገዶች የቀረቡ የፍላጎት መግለጫዎች እንጂ የቀጥታ ትዕዛዞች ላይሆኑ ይችላሉ።
ከጥቂት ዓመት በፊት የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ለማሳያነት በተዘጋጀው የሲ919 አውሮፕላን ሞዴል የአብራሪዎች ክፍል ውስጥ ተቀምጠው አውሮፕላን የማምረቱን ፕሮጀክት “የቻይና ፈጠራ የተሞላበት አንዱ ስኬት ነው” ብለው ገልጸውት ነበር።