
ከ 6 ሰአት በፊት
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሶማሊያው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ በአገራቸው ወታደሮች ላይ ጥቃት ሲፈጽም በተገቢው ሁኔታ መከላከል አልቻሉም ሲሉ ጠንካራ ትችት ሰነዙሩ።
ፕሬዝዳንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአል ሻብብ ታጣቂዎች ባለፈው አርብ ጠዋት የኡጋንዳ ወታደሮች የሰፈሩበትን ወታደራዊ ሰፍር በመውረር ጥቃት መፈጸማቸውን አረጋግጠዋል።
ሙሴቬኒ በመግለጫቸው እንዳሉት የኡጋንዳ ሠራዊት ጦር ሰፈርን የሚጠብቁ ወታደሮች ጥቃቱ ሲከፈትባቸው ተሸብረው የሚጠበቅባቸውን ባለማድረጋቸው፣ የአል ሻባብ ተዋጊዎች የተወሰኑ የጦሩን መገልገያዎች አውድመዋል።
ጨምረውም አብዛኞቹ የኡጋንዳ ሠራዊት ወታደሮች ጥቃት ከተፈጸመበት ስፍራ ወጥተው ዘጠኝ ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኝ ሌላ የጦሩ ማዕከል ሄደዋል።
በትዊተር ላይ በተሰራጨው መግለጫ ላይ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ፣ ሶማሊያ ውስጥ የተሰማሩት ወታደሮቻቸው ጥቃቱ በተሰነዘረባቸው ጊዜ ማድረግ የነበረባቸውን ባለማድረጋቸው ወቅሰዋቸዋል።
የኡጋንዳ ሠራዊት በአፍሪካ ኅብረት ስር ሆኖ በሶማሊያ ውስጥ ካሉት የጦር ሰፈሮች መካከል አንዱ በሆነው ላይ እስላማዊው ቡድን ጥቃት ካደረሰበት በኋላ ወታደሮቹ ባሳዩት ባህሪ ላይ ፕሬዝዳንቱ ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።
- ዶናት ጋጋሪው፣ የሎሚ ጭማቂ አዟሪው፣ ሰሊጥ ቸርቻሪው ጣይብ ኤርዶዋን ማን ናቸው?28 ግንቦት 2023
- ቻይና የመጀመሪያዋ የሆነውን ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላን ሰርታ ለበረራ አበቃች28 ግንቦት 2023
- ራሽፈርድ አዲስ ውል የሚፈርመው መቼ ነው? የቡካዮ ሳካ ውልስ ለምን አጭር ሆነ?ከ 9 ሰአት በፊት
ሙሴቬኒ እንዳሉት በጥቃቱ ወቅት ወታደሮቻቸው ተሸብረው ሰፈራቸውን ትተው ወጥተው ነበር። ይህም ተቀባይነት የሌለው እና በቦታቸው ቆይተው ቢሆን ኖሮ ጥቃት ፈጻሚዎቹን የመከላከል አቅማቸው ጠንካራ ይሆን ነበር ብለዋል።
በጥቃቱ በርካታ በአፍሪካ ኅብረት ስር የተሰማሩ የኡጋንዳ ወታደሮች አርብ ዕለት ቡሎ ማሬር በተባለችው የሶማሊያ ከተማ አቅራቢያ የአልሻባብ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ተገድለዋል ተብሎ ይታመናል።
ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ታጣቂው ቡድን እንዳለው፣ አርብ ጠዋት የኡጋንዳ ሠራዊት አባልት የሚገኙበትን የጦር ሰፈር መውረሩን ገልጾ ነበር።
በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮም ጥቃቱ መፈጸሙን ቢያረጋግጥም በዕለቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
በጥቃቱ ወቅት ተከታታይ ፍንዳታዎች የተሰሙ ሲሆን፣ በከተማዋ ውስጥም የአልሻባብ ታጣቂዎች ታይተዋል።
አልሻባብ በጥቃቱ በመቶዎች የሚቀጠሩ ወታደሮችን ገድያለሁ ቢልም፣ ብዙ ጊዜ ቡድኑ የሚያወጣቸው አሃዞች የተጋነኑ መሆናቸው ይነገራል። ስለደረሰው ጉዳት ከገለልተኛ ወገኖች የተባለ ነገር የለም።
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ጥቃቱን በተመለከተ ባወጡት መግለጫ ላይ በጥቃቱ የተወሰኑ መሞታቸውን ከመግለጽ ውጪ በወታደሮቻቸው ስለደረሰው ጉዳት ምንም አይነት ዝርዝር አልሰጡም።
የኡጋንዳ ጦር ሠራዊትም በአል ሻባብ ስለተፈጸመው ጥቃት ለማወቅ ዝርዝር ምርመራ እያደረገ መሆኑን ባለፈው አርብ ገልጾ ነበር።
የኡጋንዳ ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ስር ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ተሰማርቶ ቆይቷል።
በዓመታት ውስጥ አል ሻባብ በኡጋንዳ ሠራዊት ላይ ባለፈው አርብ የፈጸመውን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት በአፍሪካ ኅብረት ኃይሎች ላይ ፈጽሞ አያውቅም ተብሏል።