May 29, 2023 – Konjit Sitotaw 

Image

በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ1 ሚሊየን አንድ ጊዜ ሊከሰት የሚችለው የበቅሎ መውለድ አጋጣሚ መከሰቱ ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ባኮ ቲቤ ወረዳ ከወትሮ በተለየ መልኩ አንዲት በቅሎ ከአምስት ቀናት በፊት መውለዷን የወረዳው ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

የበቅሎዋ ባለቤት ብርሃኑ ተምትሜ፤ በ2014 የገዟትን በቅሎ ለጭነት አገልግሎት ሲጠቀሙባት መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን የበቅሎዋ ሆድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን እንዳስተዋሉ የገለጹት ብርሃኑ፤ ግንቦት 15/2015 ከቀኑ 5፡30 ላይ ውርንጭላ መውለዷን ተናግረዋል።

የበቅሎዋ መውለድ ክስተት እንዳስገረማቸውም በመግለጽ፤ ውርንጭላው አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በባኮ ቲቤ ወረዳ ግብርና ጽ/ ቤት የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ለማ አያላ፤ በቅሎ ሲወልድ አይተው እንደማያውቁ እና ክስተቱ እንግዳ እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው በቅሎ አትወልድም የሚለው እሳቤ በሳይንስ እና በባህላዊ መንገድ የታመነበት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከአንድ ሚሊየን በቅሎዎች አንዳቸው ሊወልዱ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።