May 28, 2023

ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካል አንዱ የሆነው የፍትሕ ተቋም በሕገ-መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን እና ተግባር ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

መድረኩ የተዘጋጀው የፌዴራል ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሁሉም ፍርድ ቤቶች ሥራዎቻቸውን ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲሁም በቅንጅት ለመሥራት በሚያስችለው ሰነድ ላይ ለመወያየት መሆኑን አፈ-ጉባዔው ጠቁመዋል።

የለውጥ ፍኖተ-ካርታ ሰነዱ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያር የቀረበ ሲሆን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ተጨማሪ ማብራሪያ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውይይቱ ላይም የምክር ቤቱን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል እና ከክልሎች ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተውጣጡ ፕሬዚዳንቶች እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።