አቶ ክርስቲያን ታደለ ለአቶ ታዬ ደንደአ መልዕክት ላኩ!
አቶ ክርስቲያን ታደለ እንዲህ ሲሉ ሃሳባቸውን ይጀምራሉ። ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ Taye Dendea Aredo፣
በቅድሚያ በፋሽስታዊ አገዛዙ ላይ ለሰነዘሩት ድፍረት ለተሞላበት፥ ከሞላ ጎደል መሬት ላይ ያሉ መራራ እውነቶችን ለያዘው፥ ትችት አድናቆት መስጠት እፈልጋለሁ።
እርስዎም በጽሑፍዎ ደጋግመው እንዳነሱት የጠባብ ጥቅመኞች ስብስብ በብሔር ምሽግ ተደብቆ በሕዝብ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በሚወስዳቸው ዘር ተኮር ጥቃቶች እና የዘር ፍጅት ቅስቀሳዎች የተነሳ፥ አንዳችን ያንዳችንን ቁስል በወጉ እንዳንገናዘዘብ፤ ለጋራ ነገ በአንድነት እንዳንቆም፤ በሰብአዊነት ላይ በሚፈፀሙ በደሎችና ግፎች ላይ የተባበረ ድምጽ እንዳናሰማ መሆናችን እሙን ነው።
ይባስ ብሎም ይህ ጠባብ የጥቅም ቡድን ፋሽዝምን መንግስታዊ መመሪያው በማድረግ መሰል ነውሮችን በመቃወም ትችት በሚያቀርቡ የመብት ታጋዮች ላይ የኃይል እመቃና ጅምላ እስር በመፈፀም፤ አስገድዶ ሥወራዎችንና በሕዝብ ላይ የፀጥታ ኃይሉን ወረራ በሚመስል መልኩ በማሰማራት ወገናችን የየእለት ኑሮውን በሰቀቀን እንዲያሳልፍ አድርጎታል።
የሚፈፀሙ መሰል ወንጀሎችን በብሔር ምሽግ ለመደበቅ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አይተናል። ከአንዴም ሁለቴ ሕዝብን የወንጀል ተጋሪ ለማድረግ መንግስታዊ ሰልፎችን ታዝበናል። ክቡርነትዎ እንደርስዎ ሁሉ ሌሎች የብሔሩ ልኂቃንም በስማችን ወንጀል አትሰሩ ማለት ይኖርባቸዋል። ሕዝቡም ከወንድሞቻችን ጋር አታጣሉን፤ በስማችን የድሃ ጎጆ አታፍርሱ፤ ምስኪኖችን አታስለቅሱ፤ የንፁኃንን ደም አታፍስሱ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል። ፍትኅ ወንጀሉንና ወንጀለኞችን በስማቸው ከመጥራት ይጀምራልና፥ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ፥ እንደጀመሩ «ሌቦች» ያሏቸውን ፋሽስቶችና በሕዝባችን ላይ የሚያደርሱትን ሰቆቃም በስሙ እንዲጠሩት እጠይቅዎታለሁ። በቀደመው ጊዜ ለሰላም፣ ለነፃነት፣ ለፍትኅና እኩልነት ብለው ዋጋ ከፍለዋልና፤ እርስዎን ጨምሮ መላው የአገራችን ወጣቶች የከፈሉትን መስዋእትነት ባራካሰ መንገድ፤ የአገርን አንድነትና የሕዝብን ወንድማማችነት በሚገረሰስ መንገድ፤…የሚደረጉ ፋሽስታዊ እርምጃዎች በጽኑ ልናወገዝና በአንድነት ልናስቆም ይገባል።
በዚሁ አጋጣሚ ለኦሮሞ ወጣቶችና ልኂቃን የማስተላልፈው መልእክት አለኝ። የጠባብ ጥቅም ስብስብ የሆነ ፋሽስታዊ ቡድን በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚሰራቸው በደሎች የትየለሌ ናቸው። ይህ ወንጀል ቁማርተኛ ጠባብ ቡድኑ በራሱ የሰራውና ራሱ ለብቻው ተጠያቂ የሚሆንበት መሆኑን ቢያንስ እኔ በግሌ አምናለሁ። ይሁንና ይህ ፋሽስት ቁማርተኛ ቡድን በሚፈጽመው ወንጀል ምክንያት የሰላ ትችትና ተቃውሞ ሲገጥመው ሁሌም ትችትና ተቃውሞው በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የተሰነዘረ በማስመሰል የጋራ ፀረ ፋሽስት ትግል እንዳይደረግ ሙከራዎችን ማድረጉን ቀጥሏል። የኦሮሞ ሕዝብ አገር እንዲመሩ ተሰጥቷቸው የሕዝብን አደራ ቀርጥፈው በበሉ ቁማር ፋሽስቶች አረማዊ ድርጊት እንደማይገለጽ እሙን ነው። ይሁንና በተለይ ወጣቶችና ልኂቃን በሕዝባችን ስም አትነግዱ ብላችሁ በመነሳት የብሔር መደበቂያ ምሽግ የማሳጣቱን የመጀመሪያ ኃላፊነት እንድትወስዱ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ። ሁላችንም የሕዝባችንን አንድነትና ወንድማማችነት እንዲሁም የአገራችንን ቀጣይነት በዘለቄታው ከሚጎዱ በጎ ያልሆኑ ስሜት አዘል ተሳትፎዎች በመራቅ ለጋራ ነጋችን በአንድነት እንድንቆም የአደራ መልእክት አስተላልፋለሁ።
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=788236545999417&id=100044392360812&mibextid=Nif5oz