
የዳሽን ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ባልደረባ ፀጋ በላቸው በሐዋሳ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ ኮንስታብል የኋላመብራት ወ/ማሪያም ተጠልፋ ከተወሰደች ከሳምንት በላይ ሆኗታል።
የተጎጂዋ ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ የግል ተበዳይ በቤተ ክርስቲያን ደንብ መሰረት የጋብቻ ትምህርት ከወደፊት የትዳር አጋሯ ጋር ተምረው በማጠናቀቅ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለመጋባት ቀን ቆርጠው የቤት ዕቃዎችን በማሟላት ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ ጥቃት አድርሷል በሚል በፖሊስ የሚፈለገው ተጠርጣሪ የግል ተበዳይን በተደጋጋሚ ይዝትባት እና ያስፈራራት እንደነበር አዲስ ማለዳ ከጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች መስማት ችላለች።
የግል ተበዳይ ቤተሰቦች ፀጋ ያለችበትን ባለማወቃቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከመሆናቸውም ባለፈ የተበዳይ አባት በጠና ታመው ሕክምና እየተከታተሉ ስለሚገኙ ጉዳዩ ቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ጨምረው ገልጸዋል።

ግንቦት 12/2015 የግል ተበዳይ ፀጋ በላቸው፤ ከሥራ ወጥታ ወደ ግል ጉዳይ በምታመራበት ወቅት በተለምዶው አሮጌው መነሃሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጠለፋው እንደተፈፀመባት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የመነሐሪያ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ፖሊስ አያይዞም፤ የተበዳይን ሁኔታ በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት በውል የሚታወቅ ባይሆንም ፖሊሳዊ ሥራዎችን በከፍተኛ ርብርብ እና ቅንጅት ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።
አዲስ ማለዳ ከፖሊስ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ተጠርጣሪው ተበዳይን ጠልፎ ከተሰወረ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ እና ከሐዋሳ በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው ሐገረ ሰላም ወደምትባል መንደር ይዞ እንደሄደ ለማወቅ ተችሏል። ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ መረጃው እንደደረሰው ወደ አካባቢው በስውር ቢያቀናም ተጠርጣሪ መረጃው ቀድሞ ደርሶት ስለነበር ስፍራ እንደቀየረ ታውቋል። ግለሰቡ የፖሊስን እንቅስቃሴ ቀድሞ መረጃው እንዲደርሰው የሚያደርጉ አካላት ከመኖራቸው ጋር ተዳምሮ የክትትል ሥራውን አስቸጋሪ ማድረጉንም ፖሊስ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
መረጃው የአዲስ ማለዳ ነው ።